አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 19፣2012

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጉዳይ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚገኝ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ገለጹ፡፡

በአሁኑ ሰዓት በከተማ አስተዳደሩ የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ተመዝግበው ገንዘባቸውን በባንክ ገቢ ያደረጉ ስድስት መቶ አስር ሺህ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት ከንቲባው አምስት መቶ ሰባ ሺህ የሚሆኑት በሀያ ሰማኒያ የተመዘገቡ ሲሆን ቀሪዎቹ አንድ መቶ አስር ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በአርባ ስልሳ የተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ከ1997 ዓም ጀምሮ በየዙሩ የተመዘገቡ መሆናቸውን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው ቤቶችን ገንብቶ ለባለ እድለኞች እንዳይደርሱ እንደ ችግር ከጠቀሷቸው ምክንያቶች መካከል የከተማዋ የማስተር ፕላን ችግር ፣ከኦሮሚያ ጋር በተያያዘ የይገባኛል ውዝግብ ፣የኮንትራክተሮች አቅም ማነስ እና የከተማ አስተዳደሩ ወጥነት የሌለው የግንባታ ሂደት ይገኙበታል ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በኮዬ ፌጩ አካባቢ ዕጣ የደረሳቸው ዕድለኞች ከኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ጋር በተያያዘ ውዝግብ ተፈጥሮ ያልገቡ አሉ በማለት አብራርተው ወደ ፊትም ቢሆን የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ያለውን የማስተር ፕላን ጉዳይ እስካለየ ድረስ ችግሩን መፍታት እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

ለረጅም ዓመት ክፍያ አጠናቀው የቤት ባለቤት ያልሆኑ ግለሰቦች የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች በተመለከተ ባለፈው ጊዜ የአሰራር መጭበርበር እንደነበር ጠቅሰው ጉዳዩን እንደገና የማየት ስራ እንሰራለን ብለዋል፡፡

ኢንጅነር ታከለ ኡማ አሁን ላይ ግንባታቸው ተጠናቆ ለዕጣ የተዘጋጁ አንድ መቶ ሰላሳ ስምንት ሺህ ቤቶች እንዳሉ ጠቅሰው አሁንም ከኦሮሚያ ክልል የድንበር ውዝግብ ጋር በተያያዘ ጥያቄ እየተነሳባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ቤቶችን ገንብቶ ለማስረከብ እና የመሰረተ ልማቶችን ጎን በጎን ለማስገንባት በሚል ከሀምሳ ቢሊዮን ብር በላይ የባንክ ብድር እንዳለበት ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል፡፡