አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 19፣2012

በአማራ ክልል ከተሞች በባህር ዳር ፣ደብረ ማርቆስ ፣ፍኖተ ሰላም ፣ወልድያ ፣ደብረ ብርሀን ፣ራያ ቆቦ ከተሞች ታግተው ያሉ ተማሪዎች እንዲለቀቁ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፎች ተደርገዋል፡፡

ለ2 ወራት ታግተው የገቡበት ስላልታወቁት የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ ቁጣውን የገለጸው ህዝብ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዷል፡፡

በሰላማዊ ሰልፎቹ የፌደራሉ መንግሥትም ይሁን ተማሪዎቹ የታገቱበትን አካባቢ የሚያስተዳድረው የኦሮሚያ ክልል እንዲሁም ከታገቱት ውስጥ በርካቶቹ ተወላጆች ይገኙበታል የተባለው የአማራ ክልል መንግሥት ተወቅሰዋል፡፡

መንግሥታቱ የታገቱ ተማሪዎችን ሊያስለቅቁና በጭንቅ ውስጥ ለሚገኙ የታጋች ቤተሰቦች እረፍትን ሊሰጡ ሲገባ ቸልተኛ ሆነዋል በሚል ነው በሰልፎቹ ተቃውሞ እየተሰማ የሚገኘው፡፡

በሰልፎቹ ጥር 2 በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ከታገቱት ውስጥ 21ዱ መለቀቃቸውንና ቀሪ 6ቱን ለማስለቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው የነበሩት የጠቅላይ ሚንስትር ፕሬስ ሴክሪታሪ ንጉሱ ጥላሁን ላይ ተቃውሞ ሲቀርብ ውሏል፡፡

ይኸውም ተለቀቁ የተባሉት ታጋቾች ወዴት ሔዱ በሚል ነው፡፡

50 በመቶ ድርሻውን የወሰዱት የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሴት ካቤኔዎች ሴቶች ለወራት ሲታገቱ በይፋ ስለምን አልተቃወሙም የሚሉ ቁጣዎችም ተስተጋብተዋል፡፡

ሰልፎቹ በባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሸዋ ሮቢት፣ ወልዲያ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ዳንግላ እና ሌሎችም በርካታ ከተሞች ተደርገዋል፡፡

ጥር 21ም በተመሳሳይ ሰልፎች የሚደረግባቸው ከተሞች አሉ፡፡

መንግሥት የታገቱ ተማሪዎችን እንዲያስለቅቅና ያሉ መረጃዎችን ይፋ እንዲያደርግ ጫና ለመፍጠር ያለመው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ እንደቀጠለ ሲሆን፤ መንግሥት በቸልተኝነት ሊከሰስ ይገባል ያሉ የሕግ ባለሙያዎች ክስ ሊመሰርቱበት መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች በተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን እገታ በሰላማዊ ሰልፍ አውግዘዋል፡፡

መንግስት የታገቱ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እንዲያስፈታ፣ የህግ የበላይነትንም እንዲያስከብር ሀኪሞቹ በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል፡፡

የከተማ አሥተዳድሩ ነዋሪዎችም መንግስት የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር በሰላማዊ ሰልፍ አሳስበዋል፡፡