አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 19፣2012  

የግለሰቦች ወደ ኃላፊነት መምጣትም ሆነ መውረድ ከትግራይ ህዝብ ጋር ግንኙነት የለውም ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የትግራይ ክልል ተወላጆች ገለጹ።

በቅርቡ በፌዴራል መንግስት የተደረገውን የስልጣን ሽግሽግ ተከትሎ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ሁኔታው ቅሬታ እንደፈጠረበትና ህግን ያልተከተለ ነው ሲል መግለጹ ይታወሳል።

ጉዳዩን አስመልክተው በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አባል ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሌተናል ኮሎኔል ፍስሐ በርሄ እንደሚሉት የፖለቲካ ታማኝነታቸውን ብቻ በማየት ሰዎችን ወደ ኃላፊነት የማምጣቱ ባህል የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ አካሄድ ክፉኛ ጎድቶታል።

ግለሰቦች ከስልጣን ሲወርዱ “በቆይታቸው ምን አበረከቱ?” ከማለት ይልቅ ጉዳዩን ከፓርቲ ወይም ከብሔር ጋር ማያያዝ እየተለመደ መምጣቱን ደግሞ በአስረጂነት አንስተዋል።

የክልልና የፌዴራል መንግስትን በሚመሩ አካላት መካከል የሚፈጠር ልዩነትን ወደ ህዝብ ለማውረድ የሚደረግ ጥረት አለ ብለው እንደሚገነዘቡ ገልጸው፤ ይህም የተዛባ አተያይን በግልጽ ያመላክታል ብለዋል።

በቅርቡ በፌዴራልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የተደረገው የኃላፊነት ሽግሽግ ከትግራይ ህዝብም ሆነ ከሌሎች ብሔሮች ጋር ግንኙነት አለው ብለው እንደማያምኑም ገልጸዋል።

አሁን ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ “ለውጥ አስቀጣይና ለውጥ ተቃዋሚ የሆኑ ሁለት ጎራዎች ተፈጥረዋል” ያሉት ደግሞ የትዴፓ አባል የሆኑት አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ ናቸው።

የተለያዩ አጀንዳዎችን በመጠቀም አንደኛው ወገን ሌላኛውን ለማሸነፍ የሚደረግ ሽኩቻ ጎራ በለየ የፖለቲካ ትግል ውስጥ በስፋት እንደሚታይም አብራርተዋል።

በመሆኑም በቅርቡ የተደረገውን የስልጣን ሽግሽግ ከብሔር ጋር ለማያያዝ የሚደረግ ጥረት የሚጠበቅ ነው በማለት ነው የተናገሩት።

አቶ ምኡዝ ገብረህይወት በበኩላቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ ዜጎች ወደ ኃላፊነት መውጣትም ሆነ ከኃላፊነት መውረድ የሚቀጥል ሂደት እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር በቅርቡ የተደረገው የስልጣን ሽግሽግ ከብሔርና ህዝብ ጋር ይያያዛል ብለው እንደማያምኑ ነው የተናገሩት።