አባይ ሚዲያ ዜና ጥር 20፣2012

በክርስቲያኖች ላይ ገሀድ የወጣ አድሎ እየፈጸሙ በሰላም መኖር ስለማይቻል መንግሥትም አሠራሩን እንደገና ዞር ብሎ እንዲመለከት እና አገርን እና ሕዝብን ለማስተዳደር የተቀበሉትን ኃላፊነት ሕዝብን ለማስለቀስ እና የራሳቸውን ሃይማኖት የሚያስፋፉትን ባለሥልጣናት እኩይ ድርጊት እንዲያስታግሥልን እንጠይቃለን ሲል የሐረር ሀገረ ስብከት አስታወቀ።

ሀገረ ስብከቱ በበዓለ ጥምቀት በወጡ ክርስቲያኖች ላይ ተፈጽሟል ያለውን ጥቃት አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ “መንግሥት የኢትዮጵያውያን ሁሉ መሪ፣ ፖሊስም የሕዝብ ሁሉ አገልጋይ መሆኑ ቢታወቅም በሀገረ ስብከታችን የተፈጸመው ከዚህ ተቃራኒ በመሆኑ አንዱን እየደገፉ ሌላውን ማሳደድ እንዲቆም እንጠይቃለን” ብሏል።

መግለጫው ከጥር10 -13 ቀን 2012 ዓ.ም በተፈጸመው ጥቃት የ 4 ክርስቲያኖች ንብረት መውደሙን፣ 17 ክርስቲያኖች በግፍ መታሰራቸውን፣ 246 ክርስቲያኖች በተፈጸመባቸው ማስፈራሪያ፣ ድብደባ እንዲሁም ዘረፋ ምክንያት ተፈናቅለው ሐረር በሚገኘው ደብረ አድኅኖ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ተጠልለው እንደሚገኙ አስታውቋል።

ሀገረ ስብከቱ ”በመንግሥት ሥልጣን ላይ ተቀምጠው ሕዝብን የሚከፋፍል ሃይማኖታዊ ተግባር እየፈጸሙ በሰላም አብሮ የኖረውን ሕዝብ የሚያበጣብጡ አካላትን ለሕግ እንዲያቀርብልን ”ያለው መግለጫው “ጥፋተኞች እየተለቀቁ ግፍ የተፈጸመባቸው ክርስቲያኖች ራሳቸው ከሳሽ፣ ራሳቸው ምስክር በሆኑ አካላት ለእስራት እየተዳረጉ በመሆኑ ይህ እኩይ ድርጊት እንዲቆም እንጠይቃለን “ብሏል።

“የክልሉ መንግሥት ሰሞኑን በጥፋት ላይ ተሰማርተው የነበሩትን ነውጠኞች በቁጥጥር ሥር እያዋልኩ ነው በማለት በመገናኛ ብዙኃን መናገሩ መልካም ቢሆንም ክርስቶስን አስሮ በርባንን የመፍታት አካሔድ መስተካከል እንዳለበት ለማሳሰብ እንወዳለን” በማለትም መግለጫው አትቷል፡፡

“የፌደራል መንግሥትም ሆነ የክልሉ መንግሥት ክርስቲያኖች ጥምቀትንም ሆነ ሌሎች የዐደባባይ በዓላትን ሲያከብሩ ሌሎች እምነቶች ሃይማኖታዊ በዓላቸውን በሰላም እንዲያከብሩ እንደሚያደርጉ ሁሉ ክርስቲያኖች በሰላም እንድናከብር እንዲያደርጉ እናሳስባለን” ያለው መግለጫው “ሌሎች ቤተ እምነቶች በዓደባባይ በዓል ሲያከብሩ የሚሰፍነው ሰላም ክርስቲያኖች ስናከብር የሚደፈርስበትን ምክንያት መንግሥት አጣርቶ መፍትሔ እስከሚሰጠን ጥያቄያችንን በትዕይንተ ሕዝብ ጭምር ደጋግመን ማቅረባችንን እንቀጥላለን” ብሏል።