አባይ ሚዲያ ዜና ጥር 20፣2012

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት በሁሉም ክፍላተ ከተሞች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስገንባት በመረጣቸው ሕንፃ ተቋራጮች ላይ ቅሬታ ቀረበ፡፡

በአስተዳደሩ ላይ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ሕንፃ ተቋራጮች ሲሆኑ፣ ራሱ አስተዳደሩ ባዘጋጀው የፓይለት ፕሮጀክት ተፈትነው ብቃታቸውን ያስመሰከሩ መሆናቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ቡልጋ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ብርሃኑ ገድሌ ሕንፃ ተቋራጭና ሌሎችም ተቋራጮች ለአስተዳደሩ ቤቶች ልማት ኃላፊዎች ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ተቋራጮቹ እንደሚናገሩት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት በሁሉም ክፍላተ ከተሞች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማሠራት የሙከራ ፕሮጀክቶች በማዘጋጀት ተቋራጮችን መርጧል፡፡

ፕሮጀክቱን በስምንት ወራት ውስጥ ሠርቶ የማስረከብ መሥፈርት ያቀረበው ቢሆንም፣ አሁን አቤቱታ እያቀረቡ የሚገኙት ተቋራጮች በአሥር ወራትና በተወሰኑ ተጨማሪ ቀናት አጠናቀው ማስረከባቸውን ገልጸዋል፡፡

የነበራቸውን አፈጻጸም አስተዳደሩ ማድነቁንና በቀጣይም ሊያስገነባ ላሰባቸው አንድ መቶ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንደሚመረጡ ባለሙሉ ተስፋ የነበሩ ቢሆንም፣ ሌሎች የማይታወቁና ምንም ዓይነት የሥራ ልምድ የሌላቸው ተቋራጮች መመረጣቸውን አክለዋል፡፡

ደረጃ አንድ ተቋራጮች ሳይቀሩ መመረጣቸውን፣ ትክክለኛ ፈቃድ የሌላቸውና በሐሰተኛ ሰነድ የተወዳደሩ እንዳሉም አክለዋል፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ለተቋራጮች ፈቃድ ሲሰጥ የሚያስቀምጣቸው መሥፈርቶች ቢኖሩም፣ ያንን ያላሟሉ ሁሉ ለውድድር መቅረባቸውንም በመቃወም አቤቱታ ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለጊዜው መታገዱን ገልጸው፣ አስተዳደሩ በትክክለኛው አሠራር እነሱንም በማካተት ትክክለኛ መሥፈርቱን ያሟላውን በግልጽ መድረክ አስታውቆ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ከ190 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙን እንደሰሙ ጠቁመው፣ ደላሎች ለፕሮጀክቱ ከተያዘው በጀት ሁለት በመቶ ለሚሰጡ ተቋራጮች ለማሰጠት እየተራወጡ በመሆናቸው አስተዳደሩ ይህንንም በጥንቃቄ ተከታትሎ እንዲያጋልጥና ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡