አባይ ሚዲያ ዜና – ጥር 22፣2012

ለበርካታ ዓመታት በስደት ኬንያ ውስጥ የቆዩ ከሁለት ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በፍቃዳቸው ወደ አገራቸው ሊመለሱ መሆኑን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገለጸ።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኢትዮጵያዊያኑ በራሳቸው ፍላጎት ለበርካታ ዓመታት ከቆዩባቸው የዳዳብና የካኩማ ስደተኛ ካምፖች ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚያስችላቸው ድጋፍና ዝግጅት እየተደረገ ነው።

አምባሳደሩ እንዳሉት በተለያዩ ምክንያቶች የተሰደዱት እነዚህ ኢትዮጵያዊያን ለረጅም ጊዜ በስደተኛ ካምፖቹ ውስጥ የቆዩ ሲሆኑ ከመካከላቸውም ከ40 ዓመት በላይ ከአገራቸው ወጥተው በስደት የኖሩ ይገኙባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያዊያኑን ጉዳይ ለመከታተልና አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ በቅርቡ ወደ ዳዳብና ካኩማ የስደተኞች ካምፕ አቅንተው እንደነበረ ለቢቢሲ የተናገሩት አምባሳደር መለስ፤ “ስደተኞቹን የመመለሱ ሥራ ሙሉ በሙሉ ያለምንም ጫና በራሳቸው ፍላጎት የሚከናወን ነው” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ካኩማና ዳዳብ በተባሉት የስደተኛ ካምፖች ውስጥ ባለፉት ዓመታት በፖለቲካዊና ሰብዓዊ ተግዳሮቶች ምክንያት አገራቸውን ጥለው የተሰደዱ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ይገኙባቸዋል።

የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንና ከኬንያ መንግሥት ጋር በመተባበር ወደ አገራቸው የመመለስ ፍላጎት ያላቸውን ስደተኞች ለመርዳት የሚያስፈልጉ ተግባራትን በማከናወን የመጀመሪያ ዙር ተመላሾችን በዚህ ሳምንት ማብቂያ ላይ ለመመለስ አቅዷል።

አምባሳደር መለስ እንደጠቀሱት በመጀመሪያው ዙር 85 በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከ2ሺህ በላይ ስደተኞችን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ዝግጅት ተደርጓል።

ከእነዚህ መካከል ከሰባት ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው 400 ህጻናት ይገኙበታል ተብሏል።

አምባሳደሩ አክለውም የኢትዮጵያ መንግሥትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወደ አገራቸው ለሚመለሱት ኢትዮጵያዊያን አስፈላጊ የሆነ ድጋፍ በማድረግ ወደ ቀድሞ አካባቢያቸውና ኑሯቸው እንዲመለሱ ያደርጋሉ።

በኬንያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ወደ አገራቸው ለመመለስ ፍላጎት ላላቸው ኢትዮጵያዊያን አስፈላጊ የሆኑ የጉዞ ሰነዶችን እንዳዘጋጀና ለዜጎቹ ጥያቄ ምላሽ እየሰጠ መሆኑ ተጠቅሷል።