አባይ ሚዲያ ዜና – ጥር 23፣2012

ታህሳስ 1፣2012 አ.ም በካርቱም በሱዳን ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉ ኢትዮጵያዊያን እስካሁን ከእስር አለመለቀቃቸው ታውቋል፡፡

በከተማዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንደተናገሩት ኢትዮጵያዊያኖቹ በሱዳን የኢትዮጽያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ከጠ/ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ ጋር ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ እስሩ ጋብ ቢልም ይፈታሉ የተባሉት ስደተኞች ግን እስካሁን እንዳልተለቀቁ ገልጸዋል፡፡

በሱዳን ከስምንት አመት በላይ የኖረው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ለአሜሪካን ድምጽ እንደተናገረው ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ ያጎቱ ልጅ ከሚሰራበት ቦታ በፖሊሶች ተይዞ መታሰሩን ከዚያም ፍርድ ቤት ቀርቦ የአራት ወር እስራት ወይንም የአንድ መቶ ሺህ የሱዳን ፓውንድ ቅጣት እንደተላለፈበት ተናግሯል፡፡

ግለሰቡ የአጎቱ ልጅ እንዲፈታለት በሱዳን የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኢንባሲ በአካል ሄዶ ቢጠይቅም ምንም እርዳታ እንዳላደረጉለት ይናገራል፡፡

በሱዳን የኢትዮጽያ ባለሙሉ ስልጣን አንባሳደር ሽፈራው ጃርሶ በሃገሩ ህግ መሰረት በአንድ ግለሰብ ላይ ፍርድ ከተፈረደ በኋላ መሰረዝ የሚችለው ፕሬዝዳንቱ ብቻ መሆኑንና ካልሆነ ደግሞ ለፕሬዝዳንቱ እና ጠ/ሚንስትሩ ይግባኝ ከተባለ በኋላ መሆኑን እና ይህንም አድርጎ በቃል ይለቀቁ መባሉን መስማታቸውን እና በሳምንቱ መጨረሻ አዲስ ነገር ሊኖር እንደሚችል ገልጸው ኢትዮጵያዊያኑ በኢንባሲው ላይ የሚያቀርቡትን ስሞታ አጣጥለው ከ100 በላይ የታሰሩ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ገንዘብ ከፈለው መለቀቃቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው ኢትዮጵያዊያን ያነሱት ችግር የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት መከልከል ነው ሱዳን ለኢትዮጵያ ልዩ  ፍቃድ የምትሰጥ ስትሆን በቅርቡ ግን ወረቀቱን ለማግኘት የተመዘገቡ ኢትዮጵያዊያን እንዳልተሰጣቸው የገለጹ ሲሆን አንባሳደር ሽፈራው ሲመልሱ የሱዳንን ተጨባጭ ሁኔታ በማጤን ሁለቱ ሃገራት ተስማምተው ከተለያዩ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ጋር በመሆን  በኢንባሲው በኩል ጥናት እየተደረገ መሆኑን እና በሚኒስትሮች ደረጃ ሁለቱ ሃገሮች እንዲነጋገሩ እየጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አንባሳደር ሽፈራው ባለፈው ታህሳስ 1 ከታሰሩ 100 ኢትዮጵያዊያን መካከል ከ70 በላይ የሚሆኑት አሁንም በካርቱም ኦምዱርማን እስር ቤት እንደሚገኙ አረጋግጠዋል፡፡