አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 24፣ 2012

በማዕከላዊ ጎንደር ትላንት ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት በርካታ የንግድ ሱቆች መቃጠላቸውን ሰምተናል፡፡

ከጎንደር ከተማ 13 ኪ.ሜ ላይ አካባቢ አዘዞ በአንድ ገበያ ካሉ በርካታ ሱቆች መካከል 17 የልብስና የቤት እቃዎች የሚሸጡባቸው ምግብ ቤቶች ተለይተው ጥቃት እንደደረሰባቸው የተገለጸ ሲሆን በአጠቃላይ 21 ሱቆች መውደማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በእለቱ የአዘዞ ፖሊስ ጥቃት ለማድረስ ያቀደ ኃይል እንዳለ በገበያው ቦታ በመገኘት ሱቆቻችሁን በጊዜ ዝጉ ሲል ስጋቱን መግለጹን አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ከዚያ በኋላ ጥቃት ሲሰነዘር ፖሊስ ከለላ ስለመስጠቱም ሆነ ጥበቃ ስለማድረጉ የሰማነው ነገር የለም፡፡

በጉዳዩም ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት አባይ ሚዲያ አካባቢውን የጸጥታ አካላት ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም፡፡

በአሁኑ ሰዓት መከላከያ በአካባቢው እንዳለ የነገሩን ነዋሪዎች ጥቃቱ ሀይማኖትን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ለዚህም የወደሙት ሱቆች የሙስሊሞች ብቻ ናቸው ያሉ ሲሆን እስካሁን በጉዳዩ ላይ የአካባቢው ፖሊስ የሰጠው መረጃ የለም፡፡