አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 26፣2012

የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ እድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ከ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው 527 ሼዶች የኤሌክትሪክ ኃይል ባለማግኘታቸው ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ አለመቻሉን አስታወቀ።

የመሥሪያ ቦታዎቹ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እንደሚገኙ የገለፀው ኤጀንሲው፣ ግንባታቸው ከተጠናቀቀ ከኹለት ዓመታት በላይ ቢቆጠርም የመብራት እና የውሃ መሠረተ ልማቶች ባለመሟላታቸው ሼዶቹ ያለ አገልግሎት ቆመው እንደሚገኙ ገልጿል።

ኤጀንሲው ለሼዶቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የአብዛኛዎቹን ክፍያ ቢፈፅምም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እስከ አሁን ኃይል እንዳላቀረበ አስታውቋል።

ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተደጋጋሚ አቅርበናል የሚሉት የኤጀንሲው የመሥሪያ ቦታዎች አስተዳደር ጊዜያዊ ኃላፊ ተድላ አጥናፉ፣ የአብዛኛዎቹንም ክፍያ ብናጠናቅቅም እስከ አሁን የኃይል አቅርቦት ማግኘት ባለመቻላችን ሼዶቹ ያለሥራ ቆመዋል ብለዋል።

ከኤሌክትሪክ አገልግሎትም አብዛኛዎቹ ትራንስፎርመር የሚያስፈልጋቸው ናቸው።

ትራንስፎርመሮች ከውጪ አገራት በውጪ ምንዛሬ ተገዝተው የሚመጡ በመሆናቸው፣ በኢትዮጵያ ባለው ወቅታዊ የውጪ ምንዛሬ ዕጥረት ምክያንት ኃይል ለማቅረብ አልተቻለም የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከ527ቱ የመሥክ ቦታዎች ውስጥ 419 የሚሆኑት ከኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ የውሀ አቅርቦት የሌላቸው ናቸው ተብሏል።

አንድ የመሥሪያ ሼድ ውስጥም ከአምስት እስከ 10 አባላት ያሏቸው የኅብረት ሥራ ማኅበራት መያዝ ይችላሉ የተባለ ሲሆን፣ ሼዶቹ ወደ ሥራ መግባት ቢችሉ ከ 5 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር ይቻል እንደነበር ተገልጿል።

በግማሽ ዓመቱ 1 ሺሕ 223 የሚሆኑ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ እንዲሁም የመጠቀሚያ ጊዜቸውን ያጠናቀቁ ኢንተርፕራይዞችን በማስለቀቅ ለአዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ተሰጥቷቸዋል።

የተፈጠረው የገበያ ትስስርም በአብዛኛው በመንግሥት በሚወጡ ጨረታዎች እና ግንባታ ዘርፍ ላይ የተንጠላጠሉ መሆናቸውን ኤጀንሲው አስታውቋል ስትል አዲስ ማለዳ ዘግባለች።