አባይ ሚዲያ ጥር 28፤2012

 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በይፋ የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚጀምሩት ሚያዚያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሆነ የግዜ ሰሌዳው ያመለክታል ይሁን እንጂ አንዳንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያገኙት መድረክ እያካሄዱ ያለው ቅስቀሳ ለምርጫው ፍትሐዊነት እንደሚያሰጋቸው ብዙዎች ይናገራሉ።

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በተለይ በሀረር አካባቢ ባደረጋቸው ቅስቀሳዎች ምክንያት ለሚነሳባቸው ወቀሳ የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ በቀለ ገርባ ‹‹አጭር ጊዜ በቀረው የምርጫ ጊዜ ቀርቶ ከሦስትና አራት ዓመት በፊትም ቢሆን አንድ ፓርቲ በምርጫው አሸንፋለሁ ብሎ በመነሳቱ ሊኮነን አይገባም። ፓርቲያችን በምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር እንቅስቃሴ እያደረገ አይደለም›› ሲሉ ይሞግታሉ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ በአቶ በቀለ ገርባ ሀሳብ አይስማሙም‹‹ፓርቲ ወክለው የሚወዳደሩ እጩዎች ባልተለዩበት በዚህ ወቅት አስቀድሞ ቅስቀሳ ማድረግ ህዝብን ያሳስታል የሚሉት አቶ ናትናኤል  ለምርጫው አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርና ፓርቲያቸውንም እንደሚያሳስባቸው አስረድተዋል።

ብልጽግና ፓርቲ እንደ ገዥ ህግ የማስከበር፤እንደ ተወዳዳሪም ህግ አክብሮ የመንቀሳቀስ ድርብ ኃላፊነቶችን ይዞ እየሰራ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የፓርቲው የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አወሉ አብዲ ናቸው።

‹‹ቢሮ እንከፍታለን በሚል ሰበብ የምረጡኝ ቅስቀሳ የጀመሩ ፓርቲዎች መኖራቸውን፣ከዚህም ባለፈ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ አላስፈላጊ ጽንፍ የወጡ ንግግሮች በማድረግ በምርጫው ፍትሃዊነት ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው።” ሲሉ አቶ አወሉ ሁኔታውን ይገልጹታል።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር አብዱ መሐመድ አሊ እንደሚሉት፤ ገዥው ፓርቲ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ለህዝቡ የሰራውን የልማት ሥራ ሲገልጽ ቅስቀሳ ተብሎ ይወሰዳል። እንዲህ ያለ ክፍተት ቢኖርም ፓርቲዎቹ በምርጫ ቦርድ የተቀመጠላቸውን የጊዜ ሰሌዳና ሜዳ መጣስ ግን አይገባም ሲሉ ይመክራሉ‹ቤተመንግሥት ገብተን ሀውልት እናቆማለን፣ መንግሥት እንሆናለን› የሚሉ አባባሎች የምርጫ ቅስቀሳ እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም። ሲሉም ምሁሩ ይናገራሉ።