አባይ ሚዲያ ጥር 29፤2012

በአለም አቀፍ ደረጃ እስካሁን ድረስ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 30 ሺህ 852 የደረሰ ሲሆን  638 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ ደግሞ እስካሁን ድረስ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከተላከው የ11 ሰዎች የደም ናሙና የስምንቱ ሰዎች ውጤት ከቫይረሱ ነፃ ሲሆን ሶስት ኢትዮጵያዊያን በዚሁ ቫይረስ ተጠርጥረው የደም ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ ውጤቱን እየተጠባበቀ እንደሆነም  ገልጿል፡፡

ከቻይና ዉሃን ከተማ የሚመጡ ማናቸውም መንገደኞች ወደ ለይቶ ማቆያ ማእከል እንዲገቡ የተወሰነ ሲሆን በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከቻይና የሚመጡ መንገደኞች ከሌላው መንገደኛ ጋር ሳይቀላቀሉ የሙቀት ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡

በዚህም ከቻይና ለሚመጡ መንገደኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ የኢሚግሬሽን ልዩ መስኮት መዘጋጀቱም ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ ህብረት የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ማቋረጣቸው ተቀባይነት እንደሌለው ገልጧል፡፡

የማዕከሉ ዳይሬክተር ጆን ንኬንጋሶንግ፥ እስካሁን በአፍሪካ በቫይረሱ የተጠቃ አንድም ሰው አለመኖሩን አረጋግጠዋል።

ይሁን እንጅ በሁሉም የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት ቫይረሱ ወደ ሀገራቸው እንዳይገባና ምናልባት ቢገባ በምን መልኩ መቆጣጠር እንደሚገባ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም ወደ ቻይና ቀጥታ በረራ ያላቸው አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት በረራ ማቆማቸውን ጠቅሰው፥ ይህ ተቀባይነት እንደሌለው እና ትክክለኛው መንገድ ጥንቃቄ ማድረግ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ስለዚህም ወደ ቻይና በረራ የሚያደርጉ ሃገራት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሀገራት ለቫይረሱ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመው፥ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣውን ‘በረራ መቆም የለበትም’ የሚለውን አቋም በተመሳሳይ እንደሚከተል ነው ያረጋገጡት።

“አምስት ተግባራትን በአፍሪካ ደረጃ እያከናወንን ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ የመጀመሪያው የላቦራቶሪ ምርመራን በተመለከተ ከ15 ሀገራት የተውጣጡ 15 የጤና ባለሙያዎች ሥልጠና በሴኔጋል እየተሰጠ” መሆኑን አስረድተዋል።