አባይ ሚዲያ ጥር 29፤2012

የህወሃት አመራሮች በውህደቱ ጥናት ላይ የተሳተፉ ቢሆንም በመጨረሻ ሰዓት ላይ ግን የተለየ ሃሳብ ማንሳት ጀምረው እንደነበር የብልጽግና ፓርቲ ፅ/ቤት ዋና ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱአለም ተናግረዋል፡፡

ከአራቱ ግንባር ድርጅቶች አንደኛው ወጥቻለሁ በማለት ራሱን የማግለል መብት በህገ ደንቡ የተፈቀደ በመሆኑ ዲሞክራሲያዊ መብቱ መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡

ነገር ግን እኔ ካልወሰንኩ እናንተ መወሰን አትችሉም ማለት ጸረ-ዲሞክራሲ ነው ሲሉ አቶ ብናልፍ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እከሌ ድርጅት ካልወሰነ እኔም አልወስንም እና እኛ ሳንነግራችሁመወሰን አትችሉም ማለት ከጀርባ ሌላ አሻጥር እንዳለ የሚያሳይ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ህወሃት ጉባኤ አካሂዶ ጉባኤው ውህደቱን እንደማይቀበል በደብዳቤ ማሳወቃቸው ይታወቃል በመሆኑም ሎሎች ውህደቱን የተቀበሉ ፓርቲዎች ውህዱን ፓርቲ መመስረት አለበት እንጂ አንድ ድርጅት አልቀበልም በማለቱ ፓርቲው መመስረት የለበትም የሚባለው ነገር የሚያሳምን አለመሆኑን አቶ ብናልፍ አንስተዋል፡፡

አቶ ብናልፍ አክለውም አንዳንድ ጊዜ ሆን ተብለው በሚለቀቁ ዘመቻዎች እና ነገሩን ከስሩ ባለመረዳት የሚያምታቱ ነገሮች ስለሚቀርቡ ነው እንጂ በአካሄዱ ላይ ምንም አይነት ስህተት የለበትም፡፡

ሕወሃት ለመታገል ሌላ አማራጭ ሊጠቀም በመወሰኑ እኛም የራሳችንን እንቀጥላለን በማለት ያላቸውን አቋም ገልጸዋል በማንኛውም ጉዳይ ቢሆን መታወቅ ያለበት አንድ ነገር ቢኖር የትኛውም የፓርቲ አካል የክልሉን ህዝብ ሊወክል አይችልም፤ ህዝብ እና ፓርቲ አንድ አይደሉም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ100 በላይ ፓርቲዎች እንዲኖሩ እድል የሰጠናቸው ህዝብ ይወክለኛል የሚለውን መምረጥ እንዲችል ነው ሲሉ አቶ ብናልፍ ገልጸዋል፡፡

በየክልሉ ያሉ ፓርቲዎች የየራሳቸው ሰፊ የሆነ ደጋፊ ቢኖራቸውም አንዳንዱ ደግሞ ጥቂት ደጋፊ አላቸው፡፡ ጥቂቶቹም ቢሆኑ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው መብት እንዳላቸው አቶ ብናልፍ አስረድተዋል፡፡

አንድ ፓርቲ ባጠፋው ጥፋት ህዝቡ ተጠያቂ መሆን እንደሌለበት እና መጠየቅም ካለበት ራሱ ፓርቲው ስለሆነ ህወሃት በወሰደው አቋም ተጠያቂ መሆን ያለበት ራሱ ነው ብለዋል፡፡