አባይ ሚዲያ የካቲት 02፤2012

በአፍሪካ ምርጫን ነፃ እና ፍትሐዊ እንዲሁም ሠላማዊ ማድረግን ፈታኝ ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል ቅድመ ምርጫ ላይ ያሉ አሉታዊ አስተሣሠቦች መሆናቸውን የአፍሪካ ህብረት የሠላምና ደህንነት ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር እስማኤል ቸርቡኢ ተናግረዋል።

በአህጉሪቱ የሚደረጉ ምርጫዎች ከመደረጋቸው በፊት እና በኃላ ለፀጥታ ስጋት የሚፈጥሩ መሆናቸውን የገለፁት ኮሚሽነሩ በዋናነት የምርጫ አስፈፃሚ ተቋማትን ቁመና ማስተካከል እና ማጠናከር እንዲሁም ማዘመን ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመራጮች ዘንድ ያለውም ምርጫው ኢ-ፍትሀዊ ይሆናል የሚል አሉታዊ ግምት ምርጫው ሠላማዊ እንዳይሆን የራሡ አስተዋፅኦ እንዳለው ኮሚሽነሩ ተናግረዋል በአህጉሪቱ የሚደረጉ ምርጫዎችን ሠላማዊ ለማድረግ ከግንዛቤ ማሣደግ ጀምሮ ምርጫውን አግባብነት ባለው መንገድ መምራት የሚችሉ ተቋማትን መገንባት ላይ መንግስታት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

ስድስተኛው የኢትዮጵያ ምርጫ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በያዝነው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከተለያዩ ሃገራት መሪዎች ጋር ተወያይተዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጁቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ ጋር በመሰረተ ልማት ማሻሻያ በተለይም ከወደብ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ምክክር አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጊኒው ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ጋርም በአህጉራዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአልጄሪያው ፕሬዚዳንት አብዱልመጂድ ቲቦን ጋር የምስራቅ አፍሪካን እና የሳህል ቀጠናን ትስስር ማጠናከር በሚቻልበት አግባብ ላይ ምክክር አድርገዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ጋር ደግሞ በሃገሪቱ ዘለቂ ሰላምን ማስፈን በሚቻልበት አግባብ ላይ መወያየታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በውይይታቸውም በሃገሪቱ የሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደት ላይ የተደረሰው ስምምነት እንዲተገበር በጋራ ለመስራት መስማማታቸውም ተገልጧል ከዚህ ባለፈም ከደቡብ ሱዳን በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ተፈናቅለው በኢትዮጵያ መጠለላቸውን በመጥቀስ፥ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በኢትዮጵያ ላይ በሚያሳርፈው ተፅዕኖ ዙሪያም መክረዋል።