አባይ ሚዲያ የካቲት 03፤2012

ባለፈው ሳምንት አሜሪካና የአለም ባንክ በአደራዳሪነት በተገኙበት የሶስቱ ሃገራት የውጭና የውሀ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከህግና የቴክኒክ ባለሙያዎቻቸው ጋር በመሆን ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የአገራቱ ተወካዮች የግድቡን የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው በድርቅ ወቅት፣ ለዓመታት የተራዘመ ድርቅ በሚያጋጥምበት ወቅትና ለዓመታት የተራዘመ ደረቅ ወቅት ላይ ስለሚኖረው የውሃ አሞላልን በተመለከተ መሰረታዊ መግባባት ላይ መደረሱ ተነግሯል።

የአገራቱ ሚኒስትሮችም የቴክኒክና የሕግ ቡድኖቻቸው በመሰረታዊነት መግባባት ላይ የተደረሱባቸው ነጥቦችን በማካተት እስከ ፈረንጆቹ የካቲት ወር ማብቂያ ድረስ የመጨረሻ የስምምነት ሰነድ እንዲያዘጋጁ ማዘዛቸውንም በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ አስፍረው ነበር።

የውጭና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ወደየሃገራቸው ቢመለሱም የቴክኒክና የውሃ ባለሙያዎቹ በስብሰባው ለሳምንት ያህል ቀጥለዋል።

ከሶስትዮሽ ምክክራቸው በኋላ በውሃ አሞላልና ድርቅ ማካካሻ ሰነድ ላይ ላይ ለመፈረም በነገው ዕለት ቀጠሮ በተያዘው መሰረት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ዋሽንግተን ዲሲ መግባታቸውንም አቶ ፍፁም አሳውቀዋል።

ዶ/ር ስለሺ ዋሽንግተን ከገቡ በኋላም ከግብፅ እና ሱዳን ልዑካን ጋር የተደረገውን የህግ ማዕቀፍ ድርድር ውጤት ከኢትዮጵያ ልዑካን ጋር አብረውም ገምግመዋል።

የልዑካን ቡድኑ በውሃ አሞላልና ድርቅ ማካካሻ ጉዳዮች ላይ ውይይት ቢያደርግም ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚችል ሰነድ በጋራ ማዘጋጀት እንዳልተቻለ አምባሳደር ፍፁም ገልፀዋል።

በሦስቱ አገራት መካከል በሕዳሴው ግድብ ላይ እየተደረገ ያለው ድርድር በጥር ወር አጋማሽ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም በተደራዳሪዎቹ መካከል ከስምምነት ላይ ባለመደረሱ እስከ ፈረንጆቹ የካቲት ወር ማብቂያ ድረስ ለመዝለቅ ተገዷል።

አሜሪካና የአለም ባንክ በተዳራዳሪዎች ላይ ጫና አሳድረዋል እንዲሁም ለግብፅ ወግነዋል የሚሉ መረጃዎችም ሲወጡ የነበረ ቢሆንም አቶ ፍፁም ኢትዮጵያ በጥቅሟ እንደማትደራደር አሳውቀዋል።

“ኢትዮጵያ በፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት የምታምን ሲሆን፤ በአባይ ውሃ የመጠቀም መብቷን አሳልፎ የሚሰጥ ምንም ዓይነት ስምምነት አትፈጽምም” በሚል አስፍረዋል።