አባይ ሚዲያ የካቲት 03፤2012

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከኦኤምኤን ቴሌቭዥን ጋር በዘንድሮው ምርጫ ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል በቆይታቸውም በዚህ አመት የሚካሄደው ሀገራዊ  ምርጫ ዝግጅት የህግ ማእቀፎች፣ ዝርዝር አሰራሮች እና ደንቦች ዋነኞቹ በመሆናቸው እየተሰራባቸው እንደሆነ እና የክልል ጽ/ቤቶችን እንደገና በማዋቀር የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ የሃላፊዎች ምልመላ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ለእያንዳንዱ የምርጫ ሂደት የሚያገለግሉ የሎጀስቲክስ እና የኦፕሬሽን ዝግጅቶች መከናወናቸውን ተናግረዋል የኦሮሚያ ክልል የምርጫ ጽ/ቤት ሃላፊ የጡረታ ግዜያቸው አልፎ አሁንም በሃላፊነት ላይ ይገኛሉ ተብለው የተጠየቁት ሰብሳቢዋ በህጉ መሰረት ለሁለትና ሶስት ወራት የጡረታ ጊዜያቸው ተራዝሞ እንደነበር እና አሁን ላይ ግን ቢሮው በእሳቸው እንደማይመራ ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫው ግዜ ይራዘም በሚል በርካታ ሃሳቦች የሚያነሱ ሲሆን ቦርዱ ግን እንደ ህግ አስፈጻሚ ተቋም ምርጫውን በወቅቱ የማስፈጸም ግዴታ እንዳለበት እና ፓርቲዎች በሚመሩበት ህግ ስለማይመራ የእነሱን ሃሳብ ቦርዱ ላይ መጫናቸው ተገቢነት የለውም ብለዋል፡፡

ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት ሰላም ወሳኝ መሆኑን እንደሚያምኑ  በዚህም መንግስት እና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ እና ምርጫ ቦርድም ዝግጅቱንና ያከናወናቸውን ተግባራት በማሳወቅ መንግስት እገዛ እንዲያደርግ የማሳወቅ ስራ መስራቱ ተመራጭ ነው ብለዋል ሰብሳቢዋ፡፡

በመሆኑም ግብ በሌለበት ሁኔታ ሰላም ፈጥራችሁ አሳዩን ከማለት ስራቸንን ሰርተን ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ መጣር ነው ትክክለኛው አካሄድ ብለን እናምናለን ብለዋል አንዳንድ አካባቢዎች በኮማንድ ፖስት ስር እየተዳደሩ ባሉበት ወቅት እንዲሁም የህዝቡ እንቅስቃሴ በተገታበት ሁኔታ እንዴት ምርጫውን ማካሄድ ይቻላል ተብለው የተጠየቁት ወ/ሪት ብርቱካን ከዚህ በፊት የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ጥሩ ተሞክሮ የተወሰደበት እንደነበር ገልጸው ሆኖም የጸጥታው ሁኔታ ለሂደቱ ችግር ሊሆን እንደሚችል እና ዝግጅት እንደሚጠይቅ እንዲሁም  በየአካባቢዎቹ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በሚመለከት ለመንግስት ያቀረቡት ጥያቄ አለመኖሩን አስታውቀዋል፡፡