አባይ ሚዲያ የካቲት 04፤2012

ባለፈው ዓመት የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል በቀድሞ የከተማ ልማት ሚኒስትር አቶ ጃንጥራር ዓባይና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ፣ ዕጣ የወጣባቸው የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለዕድለኞች ለማስተላለፍ የፌዴራል መንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ዕጣው በወጣበት ማግሥት በተለይ በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተገነቡበት ኮዬ ፈጬ ሳይት፣ ‹ቤቶቹ የተገነቡት በኦሮሚያ ክልልና በይዞታችን ላይ በመሆኑ ተላልፈው ሊሰጡ አይገባም› በማለት በአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ መነሳቱ ይታወሳል ተቃውሞው ከተሰማ በኋላ ከከተማ አስተዳደሩና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ የኮሚቴ አባላት የድንበሩን ሁኔታ አጣርተው እንዲያቀርቡ ውሳኔ መተላለፉም አይዘነጋም፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሰናይት ዳምጠው  የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስተላለፍ የፌዴራል መንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን ለሪፖርተር የገለጹ ቢሆንም፣ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ በተቋቋመው ኮሚቴ የውሳኔ ሐሳብ ወይም በሌላ አካል ውሳኔ ግልጽ አላደረጉትም፡፡ ቢጠየቁም ‹‹በወቅቱ የተነገረውን እናንተም ታውቃላችሁ፤›› በማለት አልፈውታል፡፡

ጉዳዩ በፌዴራል መንግሥት መያዙ ብቻ ሳይሆን ዕጣ በወጣባቸው ወቅት ግንባታቸው ተጠናቆ የነበረው 80 በመቶ ብቻ እንደነበሩ የገለጹት የቢሮ ኃላፊዋ፣ ቀሪ ግንባታዎች እየተደረጉና መሟላት ያለባቸው መሠረተ ልማቶች እየተከናወኑ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ዕጣ የወጣባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቁልፍ እንደሚሰጥና እንደሚተላለፉም አረጋግጠዋል ዕጣ የወጣባቸው የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችና አዲስ ዕጣ የሚወጣባቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሚመለከት፣ ‹‹ለሕዝብ ይፋ በምናደርግበት ሚዲያ እናሳውቃለን፤›› ብለዋል እስካሁንም አስተዳደሩ የቤቶችን ግንባታ በሚመለከት ለሕዝቡ በተለያዩ ማስታወቂያዎች ሲያስረዳና ሲያስተዋውቅ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ከዓመት በፊት ዕጣ የወጣላቸው የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕድለኞች ከነገ ዛሬ ቤቱን ተረከቡ እንባላለን ብለው ቢጠባበቁም፣ ምንም ዓይነት ጥሪም ሆነ ሌላ መግለጫ ባለማግኘታቸው አቤቱታ ተፈራርመው ለቤቶች ልማት ቢሮ ስለማስገባታቸው የተጠየቁት ቢሮ ኃላፊዋ፣ ‹‹እኔ ቢሮ የደረሰ አቤቱታ የለም፡፡ ምናልባት ለቤቶች ኮርፖሬሽን ደርሶ ከሆነ እጠይቃለሁ፤›› በማለት ስለአቤቱታው የሚያውቁት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡