አባይ ሚዲያ የካቲት 04፤2012

የኢትዮጵያ የምርጫ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ የሀገር አቀፍም ሆነ የክልል ፓርቲ አባል መሆን የሚችለዉ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለዉ ሰዉ ብቻ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረንስ (ኦፌኮ) አባል የሆነውን የአቶ ጃዋር መሃመድ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ማግኘት ጉዳይ ማስረጃ ይሰጠኝ ሲል ኢሚግሬሽን፣ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ጥያቄ አቅርቧል ቦርዱ፣ ኦፌኮ አቶ ጃዋር የኢትዮጵያ ዜግነታቸዉን መልሰዉ በማግኘት ሂደት ላይ ነኝ እያሉ ፓርቲዉ ግን ኢትዮጵያዊ የሚል የአባልነት መታወቂያ ሰጥቷቸዋል ብሏል፡፡

አሁን በስራ ላይ ባለዉ የዜግነት አዋጅ መሰረት ግለሰቡ የኢትዮጵያ ዜግነት መልሰዉ አግኝተዉ ከሆነ ይህን የሚያስረዳ ሰነድ ከደህንነት፣ኢሚግሬሽንና ስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣን አቅርብ የተባለዉ ፓርቲዉ፣ ይዘዉት የነበረዉን ሌላ ሀገር ዜግነት ስለተዉና ስልጣን ላለዉ አካል ስላመለከቱ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸዉን አግኝተዋል፤ ኢትዮጵያዊም ሆነዋል ሲልም ፓርቲዉ ቀደም ሲል ምላሽ መስጠቱ በደብዳቤው ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም ፓርቲው በትውልድ ኢትዮጵያዊ ለሆነ ሰው ኢትዮጵያዊ ዜግነትን መልሶ ማግኘትን ጉዳይ በተመለከተ ከማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን እና አካል ውሳኔም ሆነ የተለየ ሰነድ ወይም ሰርተፊኬት ማግኘቱን ህጉ አልደነገገም ሲል አስታውቋል፡፡

በሰነድ እንዲያስረዳ ምርጫ ቦርድ መጠየቁ ተገቢ አይለም ሲል ፓርቲው መግለፁንም ደብዳቤው ያብራራል በዚህ የፓርቲው ክርክር መሃል የኢሚግሬሽን፣ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ቦርዱ ጠይቋል፡፡

ማብራሪያዉም አንድ የሌላ ሀገር ዜግነት ያለዉ ትዉልደ ኢትዮጵያዊ፣የሌላ ሀገር ዜግነቱን ትቶ ኢትዮጵያ መኖር ከጀመረና ኢትዮጵያዊ ዜግነቱ እንዲመለስለት ካመለከተ ያለ ኤጀንሲዉ ዉሳኔ ወዲያዉ ሊያገኝ ይችላል ወይ የሚለዉን የሚያጠራ እንዲሆን ጠይቋል ኤጀንሲዉም እስከ የካቲት 09 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ ይስጠኝ ሲል ነዉ ምርጫ ቦርድ ጥያቄዉን በደብዳቤ ያቀረበዉ፡፡