አባይ ሚዲያ የካቲት 04፤2012

በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ የ7 ዓመት ህፃንና የ17 አመት ታዳጊን ከብት በመጠበቅ ላይ እያሉ አግቶ ገንዘብ የጠየቀው ግለሰብ የ25 ዓመት እስር ተበየነበት አገሬ የሗላሸት የተባለው ተከሳሽ፥ ሁናቸው ማስረሻ የተባለን የ17 ዓመት ታዳጊ ጳጉሜን 4 ቀን 2011 ዓ.ም አዴት ቀበሌ ከብት በመጠበቅ ላይ እያለ ካገተው በኋላ 30 ሺህ ብር እንዲሰጠው ጠይቆ 20 ሺህ ብር መቀበሉ በክሱ ተመልክቷል።

ሌኛውን የ7 ዓመት ህፃን መልካሙ ጣምያለውን ደግሞ ታህሳስ 7 ቀን 2012 ዓ.ም አዴት ቀበሌ አግቶ 75 ሺህ ብር ጠይቆ 15 ሺህ ብር መቀበሉን የክስ መዝገቡ ያስረዳል ግሰለቡ ከሳምንት በላይ ህፃኑን ለርሃብና ጥም እንዲሁም ለእንግልት በመዳረግ በዓቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶበታል።

ተከሳሽ ወንጀሉን ፈፀምክ በተባለበት ቀን አዲስ አበባ እና መተማ እንደነበረ በመጥቀስ ወንጀሉን አልፈፀምኩም በማለት ክዶ ተከራክሯል ዓቃቤ ህግም የተለያዩ ማስረጃዎችን በማቅረብ ለፍርድ ቤቱ አስደምጧል።

ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ መከላከያ እንዲያቀርብ ቢፈቀድለትም የመከላከያ ማስረጃ እንደሌለው በመጥቀስ በዓቃቤ ህግ ማስረጃ ውሳኔ ይሰጠኝ ብሏል የጠገዴ ወረዳ ፍርድ ቤትም በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ማሳለፉን ከአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ህግን ማክበጃ በመቀበል የተከሳሽን ማቅለያ ውድቅ በማድረግ ተከሳሽ ወንጀሉን የፈፀመው በስግብግብነት፣ በጦር መሳሪያ፣ በአፍቅሮ ንዋይ የሰው ልጅን ከገንዘብ በማሳነስ እንዲሁም በተደጋጋሚ የተፈፀመና ህፃናትን ለርሃብ፣ ለጥምና ለእንግልት የዳረገ መሆኑ ገልጿል።

በዚህም ተከሳሽ በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል በተመሳሳይ ከወራት በፊት በጠገዴ ወረዳ ስድስት ታዳጊዎችን ያገቱ ሽፍቶች ለወላጆቻቸው ገንዘብ ጠይቀው ባለማግኘታቸው ታዳጊዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸው አይዘነጋም በአካባቢው ያሉት አጋቾች ለጸጥታ አካላቱ አዳጋች መሆናቸውም ተገለጾ ነበር፡፡