አባይ ሚዲያ የካቲት 04፤2012

በትናንትናው ዕለት በጅማና አጋሮ ከተሞች ‘ለብልጽግና እንሩጥ’ በሚል መሪ ቃል በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተሳትፈውበታል የተባለ የድጋፍ ሰልፍ ተደርጓል የሠልፉ አላማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን መደገፍ እንደሆነ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ሠልፉ የተደረገው በትናንትናው ዕለት ኦፌኮ በጅማ ከአባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ሊያደርገው የነበረውን የትውውቅ መድረክ ከተሰማ በኋላ እንደነበር ተነግሯል የኦፌኮ የጅማ ቅርንጫፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዑመር ጣሂር እንዳሉት በጅማ ስታዲየም ሊያደርጉት የነበረው ይህ ፕሮግራም በከተማው አስተዳደር ተከልክሏል።

የኦፌኮ ህዝባዊ መድረክ ቢከለከልም በጅማ ከተማ አስተዳደርና በከተማዋ ወጣቶች የተዘጋጀው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረገ የድጋፍ ሠልፍ ግን ተካሂዷል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስል የታተመባቸው ቲሸርቶችና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን ድጋፍ የሚገልፁና የሚያወድሱ ጽሑፎች በሰልፉ ላይ ታይተዋል።

የሠልፉ ተሳታፊና አስተባባሪ የሆነው የጅማ ወጣቶች ሊግ ኃላፊ ድማሙ ንጋቱ “ለውጡ መቀጠል አለበት፤ የኦሮሞ ሕዝብ መከፋፈል፤ መሰደብም የለበትም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሌሎች የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ እንደ አገር የተወከሉ መሪዎች መከበር አለባቸው በሚል ሃሳብ ሠልፉ ተዘጋጅቷል” ሲል ያብራራል።

የሠልፉ መነሻ ሃሳብ የኦፌኮ አባል የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ በተለያየ መድረኮች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲወረፉ መሰማታቸውን ቅሬታ በመፍጠሩ እንደሆነም ጨምሮ ይናገራል በትናንትናው ዕለት ኦፌኮ በጅማ ስታዲየም ከደጋፊዎቹ ጋር ሊያካሄድ የነበረው ስብሰባ ለምን እንደተከለከለ የድርጅቱ የጅማ ቅርንጫፍ ኃላፊ ሲናገሩ ከዞኑ አመራሮች ጋር በመግባባት ሲሰሩ እንደቆዩ በማስታወስ ነገር ግን ጃዋር ፓርቲያቸውን ከተቀላቀለ በኋላ አለመግባባቶች መከሰታቸውን ያስረዳሉ።

“ጃዋር ከመጣ በኋላ ጥሩ አልነበረም። የኦፌኮ ልዑክ ወደ ጅማ ለመምጣት ከወሰነ በኋላ ደግሞ እንደ ጠላት ማሳደድ ጀመሩ” ይላሉ ትልቅ ጫና እየደረሰብን ነው ያሉት አቶ ዑመር አባላቶቻቸው እየታሰሩ መሆኑንና ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የተከለከሉት የምርጫ ቅስቀሳ ታካሂዳላችሁ ተብለው እንደሆነ የሚናገሩት ኃላፊው “እኛ የጠየቅነው የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ሳይሆን የሕዝብ ትውውቅ መድረክ ለማካሄድ ነው” ብለዋል።

የጅማ ከተማ ከንቲባ የሆኑት አቶ መኪዩ መሐመድ ቢቢሲ ጉዳዩን አስመልክቶ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ሕጉን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ጠቅሰው “ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች ቅስቀሳ እንዲያደርጉ አልፈቀደም፤ ኦፌኮ በሌሎች ዞኖች የሚያደርጋቸው እንቅስቀሴዎች የትውውቅ ሳይሆን የምርጫ ቅስቀሳ ነው” ይላሉ በዚህም ምክንያት ስብሰባውን አለመፍቀዳቸውን ገልጸዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።