አባይ ሚዲያ የካቲት 04፤2012

ከሰማይ የወረደ እሳት በከምባታ ጠምባሮ ዞን ጠምባሮ ወረዳ በአራት ቀበሌያት ውስጥ 30 የሳር ቤቶችን ማቃጠሉን የከምባታ ጠምባሮ ዞን ፖሊስ መምሪያ ገለፀ።

የከምባታ ጠምባሮ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር አብረሃም ቲርካሶ በተለይ ለዞኑ ሕዝብ ግንኙነት ጽ/ቤት እንደገለፁት በጠምባሮ ወረዳ ዱርጊ፥ ሲገዞ፥ ለዘንባራ እና ሆዶ ቀበሌያት ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ ከሰማይ ወረደ በተባለ እሳት 30 በላይ የሳር ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን 6 የዳልጋ ከብቶች እና የጤፍ ክምርም የጉዳቱ ሰለባ ሆኗል።

የእሳቱ መንስዔ በግልጽ ባይታወቅም የአካባቢው ኅብረተሰብ በተመሳሳይ ሰዓት ከሰማይ ወርዶ ጉዳት እንዳደረሰ እና ተፈጥሯዊ ነው ብለው ከመናገር ውጭ ይህ ነው ብለው የሚያቀርቡት ነገር ባይኖርም ፖሊስ ግን የእሳቱን መንስኤ እና የጉዳት መጠኑን እያጣራ መሆኑን ኮማንደር አብረሃም ቲርካሶ ገልፀዋል ሲል የከምባታ ጠንባሮ ዞን ህዝብ ግንኙነት ዘግቧል።