አባይ ሚዲያ የካቲት 07፤2012

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በደሴ ከተማ ምሽትን ተገን አድርገው እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎች እየተበራከቱ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል አስተያየታቸውን ለአሜሪካን ድምጽ የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች ወንጀሉ ከንብረት ማጣት እስከ አካል ጉዳት አለፍ ሲልም እስከሞት የሚደርስ መሆኑ አሳሳቢ ያደርገዋል ባይ ናቸው፡፡

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ነዋሪዎች ባደጉበት እና በሚኖሩበት ቤታቸው በር ላይ እንደሚገደሉ በዚህም ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን እንዲሁም በእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ እክል እየፈጠረባቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ከኋላ አንገራቸው ታንቆ ስልካቸውን እንደተሰረቁ ገልጸው የጸጥታ ሃይሉ መዘናጋቱ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

ይህ የወንጀል ተግባር በዚሁ የሚቀጥል ከሆነም ለከተማዋ ከፍተኛ ስጋት በመሆኑ መንግስት ወንጀለኞች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ እና የወሰደውንም እርምጃ እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ክፍል  ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጌታቸው ሞዬ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከተማው እየተፈጸመ ያለው ወንጀል በከተማው ያልተለመደ ከዚህ ቀደም ይታይ ያልነበረ አይነት መሆኑን እና በተለምዶ ፒያሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የ1 ሰው ህይወት መጥፋቱን እና በሌላም የከተማው አካባቢ በተመሳሳይ የሌላ 1 ሰው ህይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡

ዋና ኢንስፔክተሩ ባለፊት 15 ቀናት ውስጥ ተገድለው የተገኙት ሰዎች ቁጥር ሁለት ናቸው ቢሉም አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ግን ቁጥራቸው ከዛም በላይ ያደርጉታል ፡፡

ድርጊቱን ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች በአካባቢው ከነበሩ ሰዎች ማስረጃነት በመነሳት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና ድርጊቱን የፈጸሙ ናቸው በሚል ማስረጃዎች መሰብሰባቸውን ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡

ይህንን ድርጊት ፈጽመው ምርመራ የተደረገባቸው ግለሰቦች በደሴ እና በወሎ አካባቢ የሚኖሩ ሳይሆኑ ከሌላ አካባቢ የመጡና የተደራጁ ግለሰቦች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡