አባይ ሚዲያ የካቲት 08፤2012

በትናትና ዕለት ቅዳሜ የካቲት 7/2012 ዓ.ም በቡራዩ ከተማ በሚገኝ አንድ ሆቴል ምረቃ ላይ በፀጥታ ኃይሎች ድብደባ ደርሶብናል በማለት አርቲስቶች ለቢቢሲ ገልፀዋል ድብደባ ደርሶባቸዋል ከተባሉት መካከል አንዷ ሃዊ ኤች ቀነኒ ፊቷ በደም ተለውሶ እንዲሁም እጇ የተሰበረበት ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ነበር።

ሃዊ ኤች ቀነኒ በፀጥታ ኃይሎች ተደበደበች የተባለው እውነት መሆኑን አረጋግጣ በአሁኑ ወቅት ሃያት ሆስፒታል በህክምና ላይ እንዳለች ለቢቢሲ አስረድታለች ስለደረሰባትም ጉዳት ስትገልፅ “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፖሊሶች ወደኔ መጥተው ጭንቅላቴን በዱላ ደበደቡኝ፤ ብዙ ደም ፈሰሰኝ በድብደባው እጄም ተሰብሯል”

አክላም “ከደበደቡኝ በኋላ መሬት ላይ ጎተቱኝ፤ እናም በአካባቢው የነበሩት ጓደኞቼ አንስተው ወደ ሃኪም ቤት እንዳይወስዱኝ ሲከለክሉ ነበር “ብላለች ፖሊሶቹ ጥለዋት ከሄዱ በኋላ አንድ ግለሰብ ወደ አቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ ክሊኒክ እንደወሰዳት የምታስረዳው ሃዊ በከፍተኛ ሁኔታ ደም ይፈሳት ስለነበር፤ ክሊኒኩም ውስጥ የተሟላ ህክምና ባለመኖሩ በሪፈር ወደ ሃያት ሆስፒታል እንደወሰዷትም በስልክ ለቢቢሲ ገልፃለች።

በአሁኑ ሰዓት ግን ከህመሟ አገግማ ጥሩ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አስረድታለች ከሷ ጋር የነበሩ ሌሎች አርቲስቶች እንደተደበደቡም ሃዊ የገለፀች ሲሆን፤ ቢቢሲ ለአንደኛው አርቲስት ደሳለኝ ቤከማ በደወለበት ወቅት ህክምና ላይ መሆኑን ተናግሯል ከደሳለኝ በተጨማሪም ልጅ ያሬድ፤ እንዲሁም ሌሎች እንግዶችም ተደብድበዋል ትላለች።

ለድብደባው መነሻ ምን ይሆን? ብሎ ቢቢሲ ለሃዊ ጥያቄ ያቀረበላት ሲሆን በምላሹም “በወቅቱ ዘፍነን እየወጣን ነበር የተጠራው ሰው እየተበተነ ባለበት ወቅት ፖሊሶች ወደ ሆቴሉ መጥተው ኦነግን አሞካሽታችኋል በሚል ነው ድብደባውን የጀመሩት” ብላለች።

በቡራዩ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ምክትል ኃላፊ ኢንስፔክተር አንዋር ሁሴን በበኩላቸው በሆቴል ምረቃ ወቅት ግጭት መፈጠሩን አረጋግጠው የችግሩ መንስኤ ግን ለሆቴሉ ምርቃት በተጠሩ እንግዶች መካከል ከዘፈን ምርጫ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነ ያስረዳሉ።

“በሆቴሉ ምረቃ ወቅት እንግዶቹ ለሁለት ጎራ ተከፍለው ነበር። በነኚህ መካከል ነው ግጭት የተፈጠረው። ፖሊሶች ሁኔታውን ለማረጋጋት ነው ወደቦታው ያመሩት” በማለት ኢንስፔክተር አንዋር ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በግጭቱም ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች እንዲሁም አርቲስቶች እንዳሉ ኢንስፔክተሩ ለቢቢሲ ገልፀዋል ሃዊ “ኦነግን አሞካሽታችኋል” በሚል ነው ድብደባ የደረሰብን ብትልም ኢንስፔክተሩ ግን “ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የቡራዩ ከተማ አስተዳደርን ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ብንሞክርም ስልክ ባለማንሳታቸው ሊሳካልን አልቻለም ነገር በፌስቡክ ገፃቸው ግጭቱን አስመልክቶ ባወጡት መረጃ፤ ችግሩ የተከሰተው በቡራዩ ከተማ ገፈርሳ ቀበሌ በተለምዶ ፀርሃ ፅዮን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው።

አቶ አዲሱ በላይ የሚባሉ ግለሰብ አዲስ በሰሩት ሆቴል ምርቃት ስነ ስርዓት ላይ አርቲስቶችን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተው ነበር በስነ ስርዓቱም ወቅት እንግዶች በዘፈን ምርጫ መስማማት ባለመቻላቸው ለሁለት ጎራ ተከፍለው ግጭት መፈጠሩ እንደ መንስኤ አስፍረዋል። በግጭቱ መሃልም አርቲስት ሃዊ ኤች ቀነኒ መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰባት የፌስቡክ ገፁ ያስረዳል።

ግጭቱን በተመለከተ ምርመራ እንደሚደረግና ያነሳሱና የተሳተፉ ሰዎችም ተጣርተው ለፍርድ እንደሚቀርቡና እስካሁን ባለው በቁጥጥር ስር የዋለ እንደሌለ የአስተዳደሩ የፌስቡክ ገጽ ዋና ኢንስፔክተር አንተንህን በመጥቀስ አስፍሯል።