አባይ ሚዲያ የካቲት 08፤2012

በመንግስት የተጀመሩ የብልጽግና ጉዞዎችን ለማሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ በሶማሌ ክልል የጅጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ ነዋሪዎቹ ዛሬ በጅጅጋ ከተማ እያካሔዱት ባለው ሰልፍ ላይ የብልጽግና ጉዞን የሚደግፉ የተለያዩ መልዕክቶችን አሰምተዋል።

ዛሬ በጅጅጋ ስታዲየም በመገኘት ባስተላለፏቸው መልዕክቶችም ለውጡ የክልሉን ፍትሃዊ የስልጣን ባለቤትነትና አካታችነት ያረጋገጠ መሆኑን በመግለጽ “በህብር ወደ ብልፅግና፣ ብልፅግና ለሁሉም፣ ሁሉም ለብልፅግና” የሚሉ መልዕክቶችን አሰምተዋል።

በህዝባዊ ድጋፉ ላይ የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተገኝተው ነበር በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከተገኙት መካከል የክልሉ ሀገር ሽማግሌዎችን በመወከል የተናገሩት ገራድ አብዱልማሊክ የብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም ህዝቦች በእኩልነት የሚያሳትፍ ነው ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ እውነተኛ ፌደራሊዝምን በመተግበር የክልሉ ህዝብ በሰላም በልማትና በፖለቲካ ተሳትፎ ተጠቃሚ መሆን በመጀመሩ ሊደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል የፓርቲው ደጋፊዎችና አባላት ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ሰላሙን እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉን ህዝብ ወክለው በፓርቲው አመራርነት ለሚሳተፉ አካላት ሀገራዊና ክልላዊ የአንድነት ምሶሶዎችን እንዲጠብቁም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ወይዘሮ ሂቡ አህመድ የክልሉ ሴቶችን በመወከል በበኩላቸው እንደተናገሩት ሴቶች በፌዴራል ስርዓቱ ያገኙትን መብት አጠናክሮ ለማስቀጠል የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው ።

በመሆኑም በክልሉ የሚገኙ ሴቶች ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን እየተካሔደ ያለውን የለውጥ ጉዞ እንደሚደግፉ አመልክተዋል በጅጅጋ ከተማ እየተካሔደ ባለው በዚህ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በጅጅጋ ከተማና አካባቢው የሚገኙ በአስር ሺዎች የሚቀጠሩ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ከቀናት በፊትም በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ለብልጽግና ፓርቲ አጋርነታቸውን ያሳዩ በርካታ ሰዎች የድጋፍ ሰልፍ ማድረጋቸው አይዘነጋም ይህ ህዝባዊ ድጋፍ ከዚህ በኋላም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደሚቀጥል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ለአባይ ሚዲያ ገልጸዋል፡፡