አባይ ሚዲያ የካቲት 11፤2012

በሙስናና ሌሎች ከባድ ወንጀሎች ምክንያት በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግለሰቦች ውጭ ያሉ እስረኞች ጉዳይ ፈጣን እልባት እንዲያገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ ሰጥተዋል የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል በሙስናና ሌሎች ከባድ ወንጀሎች ተይዘው የፍርድ ሂደታቸውን ከሚከታተሉ ግለሰቦች ውጭ ያሉ እስረኞች ጉዳይ ፈጣን እልባት እንዲያገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መመሪያ ሰጡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ ከትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው የትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ አመራር አባል ዶክተር አብርሃም በላይ አመራሮቹን ወክለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል ዶክተር አብርሃም በዚህ ወቅት በተለያዩ ወንጀሎች እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በህግ ጥላ ስር መሆናቸውን አንስተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ የትግራይ ተወላጆች ተለይተው እየተጠቁ እንደሆነ በስፋት እንደሚወራ ገልጸው፤ መንግስት በእስር ላይ ያሉ የትግራይ ተወላጆችን ጉዳይ እንደገና እንዲመለከተው ጠይቀዋል የፌዴራል መንግስት በተለየ መልኩ የትግራይ ክልልን በኢኮኖሚና ልማት አሻጥር ለማዳከም እየሰራ ነው የሚል ቅስቀሳ መኖሩን ጠቁመው፤ ጉዳዩን በሚለከት መንግስት ያለውን እውነት እንዲናገር ጠይቀዋል።

የትግራይ ህዝብ በፌዴራል መንግስትና በጎረቤት አገሮች ጥቃት ሊደርስበት እንደሆነ በማስመሰል የሚሰራጭ መረጃ መኖሩንም ተናግረዋል ይህም በትግራይ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ውዥምብር ፈጥሯል ነው ያሉት።

በውይይቱ ላይ የተገኙትና ከአማራ ክልል ተወላጆች ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ያቀረቡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው ከለውጡ በኋላ አማራ ክልል ከተከሰቱ ግጭቶች ጋር ታያይዞ በህግ ጥላ ስር ያሉና ቀጥተኛ የወንጀል ግንኙነት የሌላቸው ግለሰቦች በተመሳሳይ መልኩ ጉዳያቸው እንዲታይ ጥያቄ አቅርበዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው የፌዴራል መንግስት በተለየ መልኩ ሊጠቅመው ወይም ሊጎዳው የሚፈልገው ክልል አለመኖሩን ተናግረዋል።

የትግራይ ክልልን ያገለለ ልማት ኢትዮጵያን እንደአገር ሊያበለጽጋት እንደማይችል ጠቁመው፤ ከዚህ አንጻር ትግራይ በተለየ መልኩ እየተጎዳች እንደሆነ ተደርጎ የሚወራው ስህተት ነው ብለዋል ከህግ ጥሰት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ዜጎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመዋል።

የትግራይ ተወላጆችም ከዚህ አንጻር ካልሆነ በተለየ መልኩ ለእስር አለመዳረጋቸውን ነው ያነሱት ነገር ግን በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ በሙስናና ከባድ ወንጀሎች ተይዘው የፍርድ ሂደታቸውን ከሚከታተሉ ግለሰቦች ውጭ ያሉ እስረኞች የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል ጉዳያቸው እንደገና ታይቶ እልባት እንዲያገኝ መመሪያ ሰጥተዋል።