አባይ ሚዲያ የካቲት 11፤2012

በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ባለመቻሉና ከዚሁ ጋር በተገናኘ የአገር ሀብት እንዲባክን አድርጓል ተብሎ  የሚወቀሰው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ ‹‹ኢንተግሬትድ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን›› በሚል ስያሜ በድጋሚ ሊቋቋም ነው።

ሜቴክን በድጋሚ ለማቋቋም የተረቀቀው ማቋቋሚያ ደንብ፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን የተገኘው  መረጃ ያመለክታል።

ሜቴክ ‹‹ኢንተግሬትድ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን›› በሚል ስያሜ በድጋሚ እንደሚቋቋም፣ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 25/1984 መሠረት እንደሚተዳደርም ረቂቅ ደንቡ ይገልጻል።

በሜቴክ ሥር የነበሩት የጋፋት አርማመንት ኢንጂንሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የሆሚቾ አሙኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የደጀን አቪዬሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪና ፊዩልና ፕሮፔላንት ንዑስ ኢንዱስትሪዎች የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተብለው ከወር በፊት በፀደቀ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የተቋቋሙ በመሆናቸው፣ ሜቴክን በሚተካው አዲስ ኮርፖሬሽን ሥር አልተካተቱም።

በመሆኑም የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተብሎ በተቋቋመው ሥር ባሉ ኩባንያዎች ከታቀፉት ሠራተኞች ውጪ በሜቴክ ሥር ባሉ አምራች ኩባንያዎች ሥር ተቀጥረው በሥራ ላይ የሚገኙ ሠራተኞች፣ መሥፈርቱን አሟልተው ወደ ኢንተግሬትድ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን እንደሚዘዋወሩ ረቂቅ ደንቡ ይገልጻል።

ከሜቴክ ወጥተው በቅርቡ ወደ ተቋቋመው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተጠቃለሉትን ኩባንያዎችንና ኳሊቲ ማዕከልን ሳይጨምር፣ ሌሎቹ በሜቴክ ሥር የሚገኙ ተቋማትና ዝቋላ ስቲል ማምረቻ ፋብሪካ ጋር በተገናኘ ከዚህ ቀደም የነበሩ፣ አሁንም በሒደት ያሉ ውሎች፣ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች፣ ሥራዎች፣ ተሰብሳቢ ሒሳቦች፣ ተከፋይ ዕዳዎች፣ መዛግብት፣ ሰነዶችና ንብረቶች ወደ ኢንተግሬትድ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን የሚሸጋገሩ መሆኑንም ረቂቁ ያመለክታል።

ሜቴክ ተግባርና ኃላፊነቱን ለማስፈጸም ከዚህ ቀደም ያወጣቸው መመርያዎች፣ ማኑዋሎች በሌሎች መመርያዎች ማኑዋሎች እስካልተሻሩ ድረስ ተፈጻሚነታቸው እንደሚቀጥልም ረቂቁ ይገልጻል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሥራ ላይ የሚገኘው ሜቴክ ከገባበት ቀውስ እንዲወጣና ወደ ተግባርና ኃላፊነቱ እንዲመለስ ለማድረግ ያሉበት ዕዳዎች እንዲሰረዙ፣ የባንክ ዕዳዎቹ የመክፈያ ጊዜ እንዲያራዘሙ ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን ከሪፖርተር ጋዜጣ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።