አባይ ሚዲያ የካቲት 11፤2012

”በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ጣልቃ ገብነት እንዲሁም በትግራይ ላይ ያለው ጥላቻ የማይስተካከል ከሆነ ትግራይ ራስዋን የቻለች አገር ናት ብላችሁ ልታውጁ ይገባል” ሲሉ ትግራይን ወክለው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚገኙ አባላት ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል መልዕክት አስተላለፉ።

ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት ህወሓት የተመሰረተበትን 45ኛውን ዓመት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በመቀሌ ስታዲየም ለታደሙ ሰዎች ባደረጉት ንግግር ነው።

የትግራይ ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ደብረፅዮን  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትግራይን ለወከሉ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፤ “የስልጣን ጊዜያችሁ እያለቀ ስለሚገኝ ከመበታተናችሁ በፊት ታሪክ ስሩ። በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ጣልቃ ገብነት፣ በተለይም ትግራይን በተመለከተ በመሪዎች ደረጃ የተሰጡት የጥላቻና የፀረ ህዝብ ንግግሮችን በይፋ ኮንኑ” ብለዋል።

አክለውም “ይህ የማይሆን ከሆነ ትግራይ ራሷን የቻለች አገር መሆኗን ወስኑ፤ አውጁ” ብለዋል።

“አገር በመበተን ሂደት ነበሩ ተብላችሁ በታሪክ እንዳትወቀሱ፤ ግዳጃችሁን ተወጡም” በማለት መልዕክታቸውን ለተሰበሰበው ህዝብ አስተላልፈዋል።

ዶ/ር ደብረፅዮን ከዚህም በተጨማሪ በትግራይና በኤርትራ መካከል ያለውን ታሪካዊ ዳራም እንዲሁም አሁንም ስላለው ግንኙነት ምክር አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሁለቱ ሃገራት ከተካሄደው ጦርነት በኋላ ሰላም ከመምጣቱ በፊትም የኤርትራ ተፈናቃዮችን “አቅፎ ጥላ በመሆን” ለኤርትራ ህዝብ ወዳጅ መሆኑን አስመሰክረዋል ብለዋል።

በየካቲት 11 በዓል ደግሞ የነበሩ ቅራኔዎችን ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር ደብረፅዮን የህዝብን ቀጣይነት አስምረውታል።

“መንግሥታት ፈራሾች ናቸው እና ሰላማችንን ለማስቀጠል በህዝቦች መካከል ውይይት እንዲጀመር እንፈልጋለን።” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በትግራይና ኤርትራ ህዝቦች መካከል ያለውን የቋንቋ እና ባህል ተመሳሳይነት፣ የጋራ ታሪክ እንዲሁም በደም የተሳሰሩ ከመሆናቸው አንፃር ለጦርነት የሚፈላለጉ ህዝቦች አለመሆናቸውን አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል።

ለዚህም የተለያዩ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትን በወነጀሉበት ንግግራቸው ህዝቡን የፖለቲካ አጀንዳ መደበቂያ አድርገውታልም ብለዋል።

“የትግራይ እና ኤርትራ ህዝቦችን ወደ ጦርነት ሊማግዱት የሚያስቡ ኃይሎች አሉ፤ የተጀመረውን የሰላም ሂደት ተቋማዊ በሆነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ለፖለቲካ አጀንዳ መደበቅያ እያደረጉት ይገኛሉ” ብለዋል።