አባይ ሚዲያ የካቲት 11፤2012

ከሰኞ የካቲት 9 ጀምሮ እስከ የካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ አስቸኳይ ጉባኤውን ሲያካሒድ የቆየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ባለሰባት ነጥቦች ውሳኔ እና የአቋም መግለጫ በማውጣት ጉባኤውን አጠናቋል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና 5 ጥር 24 ቀን ለ25 አጥቢያ 2012 ዓ.ም. በወጣቶች ላይ የተፈጸመውን የግፍ ግድያ፣ “ክፉ እና ጭካኔ የተመላበት ድርጊት ነው” ሲል አውግዞ መንግሥት በወንጀለኞቹ ላይ ጥብቅ ምርምራ በማድረግ ውጤቱን በሚዲያ እንዲገልጽ ጠይቋል፡፡

በቀድሞው ቀበሌ 24/18/16፣ በቅዱስ ገብርኤል እና በቅድስት አርሴማ ስም መቃኞ ቤተ ክርስቲያን የተሠራበት ቦታ፣ ቤተ ክርስቲያን ከአራት ዓመታት በላይ ከመንግሥት ጋራ እየተነጋገረችና እየተጻጻፈች የቆየችበት፣ በታቦታት እና በከበሩ ንዋያተ ቅድሳት የከበረ እንዲሁም፣ በግፍ የተገደሉት ወጣቶች ደም የፈሰሰበት በመኾኑ፣ ወደ ክብሩ ተመልሶ፣ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶበት ምእመናን በሰላም አምልኳቸውን እንዲፈጽሙበት መንግሥት መመሪያ እንዲሰጥበትም ጠይቋል፡፡

በቤተ ክርስቲያን ላይ የተሳሳተ መረጃ ለሕዝብ በማስተላለፍ እና ስሟን በማጥፋት አገራዊ ቀውስ ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ያሉት፣ የኦኤምኤን፣ ኦቢኤስ እና ኤልቲቪ ብሮድካስት ሚዲያዎች ሓላፊዎች፣ በብዙኀን መገናኛ እና የመረጃ ነፃነት ሕግ መሠረት በሕግ እንዲጠየቁ፣ በቀጣይም ከመሰል ድርጊታቸው እንዲታቀቡ እንዲያደርግ ሲኖዶሱ ለመንግሥት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

“የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እናዳራጃለን” በሚል ሕገ ወጥ እንቅስቃሴያቸው፣ ክህነታቸው ከዛሬ ጀምሮ በንሥሓ እስኪመለሱ ድረስ ሥልጣነ ክህነታቸው የተያዘባቸው እነበላይ መኰንን፣ “ተባርኮ የተሰጠን ጽላት አለ” እያሉ ሲናገሩ የቆዩት፣ ሐሰተኛ እና ምእመናንን ማደናገርያ እንደሆነ በምልአተ ጉባኤው መረጋገጡን ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ከቤተ-ክርስቲያኒቱ ሕግና ደንብ ውጭ የኦሮሚያ ቤተ-ክህነት ጽ/ቤት እናቋቁማለን በማለት በሕገ-ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱት ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮነን፣ አባ ገ/ማርያም ነጋሳ፣ መምህር ኃይለ ሚካኤል ታደሰና ቄስ በዳሳ ቶላ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ክህደት በመፈፀማቸውና ምዕመናንን በማሳሳታቸው የተሰጣቸው ክህነት የተያዘ ሲሆን፤ ግለሰቦቹ በቤተ-ክርስቲያኗ ላይ ምንም አይነት አገልግሎትም ሆነ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ልዩነት በሌለው ድምፅ ወስኗል፡፡