አባይ ሚዲያ የካቲት 15፤2012

በዚህ ዓመት ምርጫ የማይካሄድ ከሆነ የትግራይ ክልል የራሱን ውሳኔ እንደሚወስን የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር  ዶ/ር ደብረጽዮን  ገ/ሚካኤል ገለጹ፡፡

ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ይህንን ያሉት የህወሓት 45ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበርን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ዶ/ር ደብረጽዮን በመግለጫቸው በዓሉ የተለየ ትርጉም እንደነበረው በማብራራት ህወሓት ለግማሽ ምዕተ~ዓመት የተቃረበ የምስረታ በዓሉን ማክበሩ ብቅ ብለው እንደሚጠፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አለመሆኑን እና ተቋማዊ ቅርጽ መያዙን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ህወሓት የካበተ ልምድ ስላለው ጸብ አጫሪ ድርጊቶች በፌዴራል መንግስቱ ሲፈጸሙ እንኳን በትዕግስት ለማስቆምና ህግና ስርዓት እንዲከበር ለማለፍ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።  ለዚህም ከዚህ ቀደም ወደ መቀሌ መጥቶ የነበረውን የፌዴራል የታጠቀ ኃይል በማሳያነት አንስተዋል፡፡

ይህ ወደ ውጊያ ለመግባት በቂ ምክንያት ነበር ያሉት፣ ከክልሉ እውቅና ውጭ የገባውን ታጣቂው ኃይል ከኤርፖርት እንዳይወጣ በመክበብ ተልዕኮው እንዳይሳካ አድርገናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ አሁንም ሊጣሱ የማይገባቸው ቀይ መስመሮች እንዳሉ ገልጸዋል።

ዶ/ር ደብረጽዮን ህጋዊነት የለውም ባሉት የኢህአዴግ ውህደት በህዝብ ያልተመረጠ ፓርቲ የስልጣን ባለቤት አለመሆኑን አስረድተዋል።  በመሆኑም ኢህአዴግ እስከ ምርጫ ድረስ  የስልጣን ባለቤት እንደሆነም ነው የጠቆሙት።

ምርጫ ተቋም የሚገነባበት አንዱ መንገድ ነው ያሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ በምርጫ ይህ ችግር ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

“የውሳኔ ነው” ባሉት በዚህ ዓመት ሊካሄድ የታሰበው ምርጫ ከነጉድለቱም ቢሆን እንዲካሄድ እንደሚፈልጉና የማይካሄድ ከሆነ ግን ለውሳኔ የሚያበቋቸው አማራጮች በእጃቸው ላይ እንዳሉ ገልጸዋል። አያይዘውም የውሳኔያቸውን ማንነትም በጊዜው እንደሚያሳዩ አስታውቀዋል፡፡

በምርጫው የተሻለ ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴን ለማድረግ የሃሳባቸው ደጋፊ የሆኑ የፌዴራሊስት ኃይሎችን እንደሚያሰባስቡና አሁንም ጥምረቱን የሚቀላቀሉ አዳዲስ ኃይሎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡