አባይ ሚዲያ የካቲት 16፤2012

ጥር 24 ቀን 2012 አ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና 5፣ ሀያ ሁለት አካባቢ ልዩ ስሙ 24 ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ ሌሊቱን ህግን እናስከብራለን ያሉ የጸጥታ ሀይሎች በከፈቱት ተኩስ ሁለት ወጣቶች ሲገደሉ በርካቶች እንደቆሰሉና ጽላትን ጨምሮ በርካታ ንዋየ ቅድሳት እንደተወሰዱ ይታወቃል።

ዋዜማ ራዲዮ ባሳባሰበችው ሰፊ መረጃ አሁን ችግር የተፈጠረበት መሬት 17 ሺህ 115 ካሬ ስፋት ያለው ሲሆን የቦታው ህጋዊ ሰነድ ያላቸው የቦታው ባለቤትም አቶ ሪያድ ደማጅ በ1985 አ.ም ነው የገዙት፡፡

አቶ ሪያድ ቦታውን ለማልማት ካርታ ተለውጦ እንዲሰራላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም በወቅቱ የነበሩ የመንግስት ባለስልጣናት ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር ቦታውን እንዲለቁ ያግባቡዋቸው እንደነበርና መሬቱ ባለቤት እንዳለው በመንግስት ቢታወቅም ቦታው ብዙ ፈላጊ ነበረው።

ከ2000 አ.ም በሁዋላ ለቅይጥ አገልግሎት ጥቅም ላይ እንዲውል ተለይቶ የነበረው ቦታ የአረንጓዴ ልማት ቦታ ነው ተብሎ ፍጹም ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ፕላኑ እንዲቀየር ተደረገ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዚህ ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን ለመስራት ከ1988 አ.ም ጀምሮ ጥያቄን ስታቀርብ እንደነበርና ቦታው ህጋዊ ባለቤት እንዳለው ግን እንደማያውቁ ጉዳዩን እየተከታተሉ ያሉ ተወካዮች ይናገራሉ።

የቦሌ ክፍለ ከተማው መሬት ህጋዊ ባለቤት ጉዳይ ባልተቋጨበት እንዲሁም የቤተክርስቲያኗም ጥያቄ  ምላሽ ባላገኘበት ሁኔታ የማርሲል ቲቪ ባለቤት ፓስተር ዮናታን አክሊሉ በቦታው ላይ የመልካም ወጣት ማእከል ለመገንባት በዚህ አመት ታህሳስ ወር ላይ ጥያቄ አቅርቦ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተፈቅዶለታል የፓስተሩን ጥያቄ ተከትሎም ቦታው ከአረንጓዴ ልማትነት ወደ ቅይጥ አገልግሎት ተቀየረ።

ለመልካም ወጣት ማእከል ግንባታ ቦታው መፈቀዱ ውስጥ ለውስጥ ሲሰማ የቆየ ጥያቄ እያለ ለቅርብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለምን ተሰጠ በሚል የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቦታው ላይ ቤተክርስቲያን በመስራት ለምእመናን አገልግሎት መስጠት ትጀምራለች።

በይዞታው ላይ ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ ሲደረግ የመሬቱ ህጋዊ ባለቤት አቶ ሪያድ በቦታው ላይ ያለውን እንቅቃሴ በፍርድ ቤት ሊጠይቁ እንቅስቃሴ ላይ በነበሩበት በዚህ መሀል የወጣቶቹ ግድያ ተፈጸመ፡፡

ቤተክርስቲያኗ አሁን ወጣቶች የተገደሉበት ቦታ ቤተክርስቲያን እንዲሰራበት በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል ጥያቄ ብታቀርብም ዋዜማ ራዲዮ ግን መሬቱ ለአቶ ሪያድ እንዲሰጥ የመጨረሻ ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን ሰምታለች።