አባይ ሚዲያ የካቲት 18፤2012

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የፓርቲ አባል በመሆኑ በጸጥታ ኃይሎች የታሰረ ዜጋ የለም ሲል ከዚህ ቀደም የቀረበበት ወቀሳ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስታወቀ።

ባለፉት ኹለት ሳምንታት ወስጥ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባላቶቻችን ታስረውብናል ቢሉም፣ የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ የፓርቲ አባል ስለሆነ ብቻ የታሰረ ሰው የለም ሲል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

የኦፌኮ ቢሮ ኃላፊ ጥሩነህ ገመታ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ ፓርቲያቸዉ እስከ የካቲት 11/ 2012 ድረስ 27 አባላቶቹ ታስረውበታል። ከእነዚህም ውስጥ ከታሰሩ ከአንድ ወር በላይ የሆናቸዉ በምዕራብ ወለጋ ዞን የፓርቲዉ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አብርሃም ዲአና፣ ለሦስተኛ ጊዜ የታሰሩና የምእራብ ጉጂ ዞን የኦፌኮ ዋና ጸሐፊና የማእከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ጃተኒ ምትኩ ይገኙበታል። በተጨማሪ በአምቦ አካባቢ 25 አባሎቻቸዉ ያለአግባብ እስር ላይ መሆናቸዉን ጥሩነህ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር ባሳለፍነዉ ኹለት ሳምንታት ብቻ ከ400 በላይ አባላቶቹ እንደታሰሩበት የፓርቲዉ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሚካኤል ቦረን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አባሎቹ የታሰሩት በባሌ፣ በምዕራብ ሐረርጌ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ፣ በአምቦ፣ በቡራዩና በመቱ እንደሆነ ሚካኤል አክለዉ ገልፀዋል።

በተቃራኒው የኦሮሚያ ክልል የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ጌታቸው ባልቻ፣ በክልሉ የኦፌኮም ሆነ የኦነግ የፓርቲ አባል ስለሆነ የታሰረ ሰው እንደሌለና የፓርቲ አባል ስለሆነ የታሰረ ሰው ስለመኖሩ ክልሉ መረጃ እንደሌለዉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። እንደ ኃላፊው ንግግር፣ የታሰሩ ሰዎች ካሉም በሠሩት ወንጀል እንጂ የፓርቲ አባል ስለሆኑ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ ማክሰኞ የካቲት 10/2012፣ የጨፌ ኦሮሚያ 5ኛ ዓመት መደበኛ ስብሰባ ባካሄደበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ራሳቸውን ነጻ አውጪዎች ነን ብለው የሰየሙ ሽፍቶች በኅብረተሰቡ እና በመንግሥት መዋቅር ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ መንግሥት እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን መግለጻቸው ይታወሳል።