አባይ ሚዲያ የካቲት 21፤2012

በድሬደዋ የጋራ መኖሪያ ቤት ቆጣቢዎች ቅሬታ አነሱ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በ2012 የበጀት አመት ይተላለፋሉ ከተባሉት ሁለት ሺ ቤቶች ውስጥ 353ቱን ብቻ ማስተላለፉ ለአመታት ገንዘብ ሲቆጥቡ የነበሩ ከስድስት ሺህ በላይ ነዋሪዎችን አስቆጥቷል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ከ2008 ጀምሮ የቤት ባለቤት ለመሆን ከ15 ሺ በላይ ሰዎች ገንዘብ ሲቆጥቡ የቆዩ ሲሆን በ2012ም ላለፉት ስድስት ወራት ቁጠባ ያቋረጡ ሰዎች ከእጣ ውጪ በማድረግ ለስድስት ሺህ ነዋሪዎች ለማውጣት ዝግጅት እየተካሄደ ነው፡፡

ነገር ግን በ2011 ግንባታቸው ተጀምረው በተያዘው ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብለው ከሚጠበቁት ሁለት ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ አምስት በመቶው ብቻ ተገንብቶ ለመተላለፍ ተዘጋጅቷል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በገባው ቃል መሰረት ቤቶችን ገንብቶ ለማስተላለፍም ከፌደራል መንግስት ብድር ሲያቀርብ ነበር የሚሉት የድሬደዋ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ የቤት ማስተላለፍ እና ማስተዳደር ሃላፊ አዲና መሀመድ ድጋፎች በመቆሙ ምክንያት አስተዳደሩ እነዚህን ቤቶች በራሱ በጀት መገንባቱን ገልፀዋል፡፡

ቤቶቹ ለተጠቃሚዎች በሚተላለፉበት መንገድ ላይ በርካታ ጥያቄዎች እየቀረቡ እንደሚገኙ ገልፀው የከተማ አስተዳደሩ ያለማቋረጥ ሲቆጥቡ ከነበሩ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች በእጣ እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት የቤቶችን ካርታ ሰርተፊኬት ወደ ዳታ ቤዝ የማስገባት እንዲሁም ካርታ ላልነበራቸው 1ሺ 109 ቤቶች ውስጥ 418 የሚሆኑትን የይዞታ ማረጋገጫ እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡

አስተዳደሩ በቀጣይ 20ሺ መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ለያዘው አቅድ ከፌደራል መንግሰት ብደር እንዲያገኝ እና አሁን በአስተዳደሩ በጀት እየተገነቡ የሚገኙ ቤቶች ክፍያ ከባንክ ጋር እንዲተሳሰር ማድረግ እንደሚገባ አስተዳደሩ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የድሬደዋ አስተዳዳር ቤቶች ኮርፖሬሽን በበኩሉ በራካታ ያለተከፈሉ ውዝፍ እዳዎችን የማስከፈል፣ በህገወጥነት የተያዙ ቤቶችን የማስመለስ ከእገዳ በፊት የኮርፖሬሽን መመሪያ ለደንበኞች ቀድሞ የማስተዋወቅ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ በገቢ እራሱን እንዲችል እንዲሁም ህገወጥትን ለማስቀረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡