አባይ ሚዲያ የካቲት 21፤2012

በትላንትናው እለት በራያ ዋጃ ከተማ የህወሓት የጸጥታ አካላት በጥቂቱ የ7 ሰዎች ቤት ማፍረሳቸውን የራያ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደጀኔ አሰፋ ለአባይ ሚዲያ ገልጸዋል።

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር/ትህነግ የሚስኪኖችን እና የድሆችን ቤት ያለ ህዝብ ይሁንታና ምክክር በታጣቂዎቹ ታጅቦ እያስፈረሰ ነው ሲሉ የኮሚቴው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ በትላንትናው እለት የዋጃ እናቶች አልቅሰዋል፤ አባቶች አንገታቸውን ደፍተዋል፣ ህፃናት መጠግያ ማረፍያ አጥተዋል፣ ህዝቡም ግራ ተጋብቷል፣ በጠራራ ጸሃይ መኖርያ ቤቶች በታጠቁ ኃይሎች ፈርሰዋል ሲሉ አቶ ደጀኔ አክለዋል።

ተወላጆችን ከቀያቸው ለመንቀል ህዝቡ ሳያምንበት በግዳጅ ቤታቸውን እያፈረሰ የዲሞግራፊ ለውጥን ለማሳካት የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር/ትህነግ የመሬት ወረራውን ተያይዞታል፣ የራያ ህዝብ የሚደርስለት መንግስት አጥቷል፣ ሲሉ በራያ ህዝብ ላይ ግፍ መብዛቱን እንዳሳዘናቸው አቶ ደጀኔ አብራርተዋል የዋጃ ከተማ አስተዳደርና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።