አባይ ሚዲያ የካቲት 23፤2012

124ኛው የዓድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ ከተማ ሚኒሊክ አደባባይ ከፍተኛ የስራ ሓላፊዎች ፣ አባት እና እናት አርበኞች እንዲሁም በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት በድምቀት የተከበረ ሲሆን ድሉን የሚያስታውሱ ትዕይንቶችም ቀርበዋል፡፡

በዓሉ የጣሊያን ወራሪ ድል በተደረገበት የዓድዋ ተራሮች ስርም በተለያዩ ስነ ስርዓቶች የተከበረ ሲሆን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤልና ሌሎች የፌደራል እና የትግራይ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በዓድዋ ድል ምክንያት ኢትዮጵያውያን የአይበገሬነትና የነፃነት ተምሳሌት መሆን ችለዋል ያሉ ሲሆን ቀደምቶቻችን በዓድዋ ድል ማድረግ የቻሉት መደማመጥ እና መቻቻል፣ ትናንሹ ላይ ሳይሆን ትላልቁ ላይ ማተኮር በመቻላቸው ነው ብለዋል፡፡

በአንድነት ከቆምን ምንም እንደማይሳነን ከዓድዋ የድል ታሪካችን መማር ይገባናል ያሉት ፕሬዝዳንቷ ድሉ ምንም ልዩነት በመካከላችን ቢኖር በሉዓላዊነታችን የማንደራደር መሆናችንን ያሳየ ነው በዓድዋ የድል ታሪካችን መኩራታችን ተገቢ ነው፤ ከዚሁ ጎን ለጎን ግን በአሁኑ ወቅት አንድነታችንን የሚፈታተኑ ጉዳዮች መኖራቸውንም መረዳት ይገባናል፡፡

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ አክለውም ሀገራችን የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጋራ የተሳፈርንባት ጀልባ እንደማለት ናት፤ የሁላችንም ሕልውና የተመሰረተው በጀልባዋን ደህንነት ላይ ነው፤ የጀልባዋን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ችግር ሲከሰት ልንታገሰው አይገባም ብለዋል፡፡

በማህበራዊ ገጻቸው መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የአድዋ ድል በብርቱ ትግል የተገኘ ነጻነትና የአፍሪካን መጻኢ ዕድል በኅብረት እውን ማድረግ እንደምንችል ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

የአድዋ ድል ብሔራዊ ድል ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአፍሪካን ነጻነት መልሶ የወለደ ድል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹በዓድዋ የተሠራው ድል የብዙ ትምህርቶች ምንጭ የሆነ፣ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ፋይዳ ያለው ታሪካዊ ድል ነው›› ያሉት ደግሞ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅጽዮን ገ/ሚካኤል ናቸው፡፡

ዓድዋ አባቶቻችን እና አያቶቻችን ለሀገራችን ጥቅም ሲሉ ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው አውቀው ለጦርነት በመሰለፍ ያሸነፉበት ነው ያሉት ዶ/ር ደብረፅዮን ድሉ ለውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት እንደማንበረከክና ለነፃነታችን ስንል የማንከፍለው ነገር እንደሌለ ያሳያል›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የቀረበውን የውል ሰነድ ከውጫሌ ውል ትምህርት በመውሰድና በውሉ የሚሰፍሩ ቃላት በሉዓላዊነት ላይ ችግር እንዳያስከትሉ በከፍተኛ ጥንቃቄና ኃላፊነት መመዘን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የብልፅግና አመራሩ አቶ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው በዓሉን እጅግ በጣም ታሪካዊ የጥቁሮች ሁሉ የኩራት ቀን ብለውታል ኢትዮጵያዊያን ተደምረዉ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጭ በጥቁር ሊሸነፍ እንደሚችል ለአለም ያሳዩበት ነው ያሉት አቶ ታዬ ታሪክንና አመለካከትን የሚቀይር አቅም የታየበት ነው ብለዋል፡፡