አባይ ሚዲያ የካቲት 25፤2012

የኢትዮጵያ መንግሥት በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ያሳየውን አቋም እንደሚደግፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ፡፡

በሀገሪቱ እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአሜሪካ ግምጃ ቤት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ውኃ ከመሙላትና የሙከራ ሥራ ከመጀመሩ በፊት በሦስቱ ሀገራ መካከል ስምምነት መፈረም እንዳለበት መግለጫ ማውጣቱ ተከትሎ እስካሁን ኢዜማ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኅብረት (ኢዴኅ)፣ የዓሲምባ ዴምክራሲያዊ ፖርቲ (ዓዴፓ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን)፤ አብን፤ ምክክር ፓርቲን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች መግለጫውን አውግዘዋል፡፡

የኢዜማ ሊቀ መንበር የሺዋስ አሰፋ ኢትዮጵያ ዓባይ ወንዝን የመጠቀም ተፈጥሯዊ፣ ሕጋዊ እና ታሪካዊ መብት እንዳላት ገልጸው ይሁን እንጂ የግብጽ እና የአሜሪካ ግምጃ ቤት አቋም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት የሚጋፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሊቀ መንበሩ በኢትዮጵያ ላይ የዓለም ፍርደ ገምድልነት በተደጋጋሚ መስተዋሉንም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ኅብረት ምክትል ሊቀ መንበር  ገብሩ በርሄ ደግሞ “የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የሚከለከል እና የሚያስቆም ኃይል የለም” በማለት መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዲቆሙም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የአዴኃን ሊቀ መንበር ተስፋሁን ዓለምነህ በበኩላቸውአሜሪካ እና የዓለም ባንክ ቀደም ሲል በታዛቢነት ከዚያም ከአደራዳሪነት አልፎ ወደ ውሳኔ ሰጪነት መሸጋገራቸው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ በመሆኑ ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲመጣ ኢትዮጵያ በትኩረት ልትሠራ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ አደራዳሪ (በተለይም አሜሪካ እና የዓለም ባንክ) እንዲኖር መፈቀዷን እና ከሦስቱ ሀገራት ውጪ አሜሪካ ሄዳ ድርድር ማድረጓ መሠረታዊ ስህተት እንደነበር የፓሪቲዎቹ ተወካዮች ተናግረዋል፡፡

ቢሆንም ስህተቱን ለማስተካከል መሞከሩን በጥሩ ጎኑ ተመልክተውታል፡፡

ድርድሩን ከማዘግየት ባለፈም ቀጣይ በጉዳዩ ላይ የሚደረጉ ውሳኔዎች በተገቢው መንገድ ተጠንተው መሆን እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡

ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ በሂደት ላይ ያለውን ውይይት መንግሥት በሀገር ወዳድነት የሚወስደዉን ርምጃ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በኅብረት ሊደግፈዉ እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

መንግሥትም የሚወስዳቸውን ርምጃዎች ሁሉ በግልፅነት ከሕዝብ ጋር እንዲመከርም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡