አባይ ሚዲያ የካቲት 25፤2012

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የተለያዩ ወንጀሎችን ሰርተው በብሄር፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በተለያዩ ቡድኖችና በየክልሎቹ የተደበቁ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውላለሁ እያለ ነው፡፡

በመስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ መያዣ ወጥቶባቸው በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተጠርጣሪዎችን ጭምር በህግ ፊት ለማቅረብ ስራ ጀምረናል ይላሉ፡፡

ዳይሬክተሩ፤ የክልል የጸጥታ አካላት በአካባቢያቸው በተለያዩ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በህግ ፊት ለማቅረብ ኃላፊነቱን ወስደው ተጠርጣሪዎች እንዲያዙ የማድረግ ስራዎች ላይ በስፋት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ ግጭቶች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ከተጠረጠሩ ከሶስት ሺ 606 ግለሰቦች ውስጥ አንድ ሺ 682 የሚሆኑትን በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ በቁጥጥር ስር ያልዋሉትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በቁጥጥር ስር ውለው ለህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራ መንግሥት ከወትሮው በተለየ ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በከባድ የሙስና ወንጀል፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በግድያ፣ ማንነትን መሰረት ባደረጉ ዘረፋዎች፣ በአስገድዶ መድፈር፣ በኃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት ያደረሱ እና የብሄር ግጭት ለመፍጠር በቀጥታ ሲሰሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በሙሉ በቁጥጥር ስር በማዋል በህግ ፊት ለማቅረብ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት በጋራ ጠንካራ አቋም ይዘው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህ በአንዲህ እንዳለ የቀድሞው የጠቅላይ አቃቢ ህግ ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና አቶ ብርሃኑ ጸጋየ ትላንት የአምባሳደርነት ሹመት እንደተሰጣቸው ሲሰማ የተለያዩ ለፖለቲካው ቅርብ የሆኑ ምሁራን በቀድሞው ኢህአዴግ  ዘመን እንደነበረው ባለስልጣናት የተሰጣቸውን ከፍተኛ ሃላፊነት ያልተወጡ ግለሰቦች ከሃላፊነት የተነሱበት ምክናየት ግልጽ ሳይሆን አምባሳደር እየተደረጉ የሚሾሙበት ሂደት አሁንም መቀጠሉን ተችተዋል፡፡

ጠቅላይ አቃቤ ህግ በየክልሎቹ የተደበቁ ወንጀለኞችን እይዛለሁ ቢልም በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የእስር ማዘዣ የወጣባቸው አቶ ጌታቸው አሰፋ ዛሬም ድረስ የህወሃት አመራር ሆነው በህወሃት ምስረታ በዓል ላይ ሽልማት የተበረከተላቸው መሆኑ ብዙዎችን ከማስገረሙም በላይ በብልጽግናና በህወሃት መካካል ያለው ተቃርኖ ትግራይ ክልል ያሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ቀላል እንደማይሆን ማሳያ እንደሆነ ይነገራል፡፡