አባይ ሚዲያ የካቲት 25፤2012

የህወሓት ስራ~አስፈጻሚ አባል ጌታቸው ረዳ ከለውጡ ወዲህ በተለያዩ የትግራይ ሚዲያዎች ብቅ እያሉ ሃገራዊ ለውጡንና ለውጡን እየመራው እንደሆነ የሚታወቀውን አካል እንደሚያጣጥሉ በተደጋጋሚ ታይቷል።

የህወሓት ጉዳይ ገዳይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ ጌታቸው በትላንትናው ዕለትም እንደለመዱት በትግራይ ሚዲያ ሃውስ ቀርበው ጸቤ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ሳይሆን የብልጽግና ፓርቲ ህጋዊነቱን ሳያሟላ ህጋዊ ነህ ካለው የምርጫ ቦር ጋር ነው ሲሉ ምርጫ ቦርድን ወቅሰዋል።

ይሁን እንጅ የምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት ዋና ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ኢህአዴግ በስራ~አስፈጻሚ አባላቱ መፍረሱን አውጆ ብልጽግና የመሰረተው ህጉን ተከትሎ እንደሆነ ገልጸው ህወሓትም ንብረት አካፍሉን ከማለት ባለፈ ኢህአዴግ ለምን ፈረሰ የሚል ቅሬታ አለማቅረቡን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የብልጽግና ፓርቲን ከፊውዳልና ደርግ ስርአት ጋር ያመሳሰሉት አቶ ጌታቸው ግን ፓርቲው በትግራይ ክልል ውስጥ ተወካዮቹን የመረጠበት መንገድ አጼ ኃይለስላሴ ይረብሹኛል ያሏቸው ሽፍቶችን አስጠርተው የግራዝማችና ባላምባራስነት ማዕረግ በመስጠት ቀሚስ አልብሰው ከሚልኳቸው ተመራጮች በታች ነው ሲሉ ብልጽግናን አናንቀዋል።

የኢኖቬሽን ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ የትግራይ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ሆነው መመረጣቸውን የመተዋወቅ ምርጫ ሲሉም አጣጥለዋል።

የምርጫው ሂደት በልጅነት ላይ የምንጫወተውን ፖሊስና ሌባ ከምንመራረጥበት ሂደት አይሻልም ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ሂደቱም ገና በክፍል አንድ እያለ የሞተ ቀሽም ድራማ ነው ብለውታል።

አቶ ጌታቸው ረዳ የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙሪያ የሰጡትን አስተያየት ተከትለው መግለጫው የቀጠናው ፈርኦን የመሆን ፍላጎት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

ይሁንና ፕሬዝደንት ኢሳይያስ መፍራት ካለባቸው ከትግራይ ውጭ ያለውን አካል መሆን እንዳለበት ይናገራሉ።በኢትዮጵያ ጉዳይ እጄን አጣጥፌ አላይም ያሉት ፕሬዝደንት ኢሳይያስ በጸሎት ወይ በምህላ ሊያግዙን አይደለም ሲሉ አቶ ጌታቸው፣ ዶ/ር ዐቢይ በዚህ ዙሪያ ምላሽ አለመስጠታቸውን ወቅሰዋል።

በሌላ በኩል ምርጫ የችግሮች ሁሉ መፍትሄ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ የተናገሩት አቶ ጌታቸው ምርጫው መካሄድ እንዳለበት ግን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በአነጋጋሪነታቸው የሚታወቁት አቶ ጌታቸው ረዳ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንደሚያሰጋቸው ገልጸው በትግራይ በኩል የህዝብን ጥያቄ በመመለስ ጤነኛ ብሔርተኝነት በማስቀጠል የትግራይ ህዝብ ህልውና እናረጋግጣለን ብለዋል።

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ባለፈው ባሌ ላይ ግድብ ሲያስመርቁ 27 ዓመት የሰበሩንን ሰብረናቸዋል፣ ዛሬ ያለኛ ፈቃድ አይንቀሳቀሱም ሲሉ የህወሓት ባለስልጣናትን በግልጽ ሲያናንቁ መደመታቸው አይዘነጋም።