አባይ ሚዲያ የካቲት 28፤2012

አሜሪካም ሆነ ግብጽ እንዲሁም የዐረብ ሊግ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ፍጹም ተቀባይነት የሌለውን ኢ-ፍትሐዊ አቋማቸውን ሊያርሙ እንደሚገባ በአማራ ክልል የምሁራን መማክርት ጉባኤ አሳሰበ፡፡

የምሁራን መማክርቱ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ድህነትን አጥፍቶ ከበለጸጉት ሀገራት ጎን ለመሰለፍ ተፈጥሮ የለገሰቻትን ሀብቶቿን ዘላቂ ልማትን በሚያረጋግጥ መልኩ ለመጠቀም አቅሙ እና ችሎታው እስካለ ድረስ ይህን ለማድረግ የማንም ይሁንታ እና ፈቃድ አያስፈልጋትም ሲል መግለጫው አትቷል፡፡

ከወራት በፊት በግብጽ ጠያቂነት በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት የታላቁን ሕዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል አስመልክቶ ተጀምሮ የነበረውን ድርድር ተከትሎ በአሜሪካ እና በግብጽ የተራመደው አቋም  ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ሆኖ እንዳገኘውም መማክርቱ አስታውቋል፡፡

ምንም እንኳን አለመግባባቶችን በውይይት እና በድርድር መፍታት ተገቢ ቢሆንም የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ግንባታና የውኃ አሞላል እንዴት ማከናወን እንዳለባት የዓለም አቀፍ መርሆችን ተከትላ መወሰን ያለባት ኢትዮጵያ መሆኗ እየታወቀ ከዚህ በተቃራኒ የግብጽን ኢ-ፍትሐዊ ፍላጎት ብቻ ታሳቢ ያደረግ የውኃ አሞላል ሂደት እና ጊዜ ያስቀመጠ ስምምነት ‹‹ኢትዮጵያ ልትፈርም ይገባል›› መባሉ ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ያላትን ቋሚ ሉዓላዊ መብት የሚጥስ ከመሆኑም በላይ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስሜት ያለበት፣ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መንፈስን እና መርሆችን የሚቃረን፣ ዓለማቀፍ ትብብርን የማያጎለብት እና በቀጠናው ባሉ ሀገራት መካከል ያለው ሠላማዊ ግንኙነት እንዲሻክር በር የሚከፍት መሆኑን ተገንዝበናል ሲል መግለጫው ያትታል፡፡

በተጨማሪም የዐረብ ሊግ ግድን አስመልክቶ ግብጽን በጭፍን በመደገፍ ያወጣው ፍርደ ገምድል መግለጫ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ መብት እና ሉዓላዊነት የሚጋፋ ሆኖ አግኝተነዋል፤ ስለሆነም አሜሪካም ሆነ ግብጽ እንዲሁም የዐረብ ሊግ ፍጹም ተቀባይነት የሌለውን ኢ-ፍትሐዊ አቋማቸውን ሊያርሙ ይገባል ሲል መማክርቱ አቋሙን ገልጧል የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ጠንካራ የዲፕሎማሲ አቅም የሚጠይቅ መሆኑን ተረድቶ ተቀባይነት የሌለውን የሁለቱን ሀገራት አቋም ለማስቀየር የተደራጀ እና ሁሉን አቀፍ የሆነ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ትግል እንዲያደረግ በአጽንኦት ያሳሰበ ሲሆን የምሁራን መማክርት ጉባኤው አስፈላጊውን ሙያዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጧል፡፡