አባይ ሚዲያ የካቲት 30፤2012

በሀገሪቱ ደቡብዊ ክፍል ከአዲስ አበባ በ85 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ከዋናው አስፓልት መንገድ ወደ ውስጥ አምስት መቶ ሜትር ገባ ብሎ ይህ ታሪክ ተቀምጧል።

ይህ ለኢትዮጵያ ድንቅ ለአለም ትልቅ ሀብት የሆነው በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው የጥያ የመካነ መቃብር ትክል ድንጋይ መገኛ ስፍራ ነው።

ሀገሪቱ ካሏት በአለም ቅርስነት ከተመዘገቡ ውስን ውድና ድንቅ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነውና ቁጥራቸው 40 የሚደርሱት የጥያ ትክል ድንጋዮች በእንክብካቤና ጥበቃ ጉድለት ስጋት ላይ ወድቋል።

በትክል ድንጋዮቹ ላይ የተቀረፁ ምልክቶች ደብዝዘው፤ በፀሀይና ዝናብ ቀድሞ የነበራቸው ይዘትና ቅርፅ አጥተዋል፡፡

የመስህብ ጥናት ባለሙያው አቶ ሽመልስ ተስፋዬ ‹‹ቅርሱ በአግባቡ ተጠብቆና ወደነበረበት መመለስ ካልተቻለ ከአለም አቀፍ ቅርስነት የመሰረዝ እድል ሊገጥመው ይችላል›› በማለት ስጋታቸውን ይናገራሉ።