አባይ ሚዲያ የካቲት 30፤2012

ኢትዮጵያ ጥቅሜን ይጎዳዋል ባለችውና በአሜሪካ እንደቀረበ በሚነገርለት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የስምምነት ሰነድ ላይ እንደማትፈርም ካሳወቀች በኋላ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በመግለጫ መወዛገባቸውን ቀጥለዋል በተለይም በአሁኑ ወቅት በህዳሴ ግድቡ ግንባታና በድርድሩ ሂደት የግብጽና የሱዳን አቋም ተቃርኖ ውስጥ ገብቷል፡፡

አልጀዚራ ትላንት ምሽት ከግብጽና ከሱዳን የሆኑ ሁለት እንግዶችን አቅርቦ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሰንዝሯል ከሱዳን በኩል የተጋበዘው ዶክተር ዲሊ አልከባሽ የተባለ የሱዳን መንግስት አማካሪና በካርቱም ዩንቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ነው።

ዶክተር ዲሊ ኢትዮጵያ ምንግዜም በራሷ የምትተማን ሃገር ናት፤ ለማንም እውነት ነው የአረብ ሊግ ያወጣው መግለጫ በጣም አሳፋሪና በኢትዮጵያ ላይ መድሎን የሰራ ለግብፅ ያዳላ ነው ሲሉ ተደምጠዋል አክለውም ሱዳን በአረብ ሊግ ላይ የወሰደችው አቋም አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው ያሉ ሲሆን ይሄንን ውሳኔ ባንወስን ኖሮ የሱዳን ህዝብ በመንግሥት ላይ ተቃውሞ ያደርግ ነበር  ሲሉ ይገልጻሉ።

ግብፃዊው የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ሁሴን አብዱራዲ በበኩላቸው የአባይ ውሃ ለግብፅ ህዝብ የህልውና ጉዳይ ነው፤ የግብፅ መንግስት እያደረገ ያለው ግብፅ በአባይ ላይ ያላትን ታሪካዊ የመጠቀም መብትን መቶ በመቶ እውን ማድረግ ነው በማለት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጊዜ ክህደት እየፈፀመች ነው በሚል ወንጅለዋል።

ፖለቲከኛው አክለውም በቅርቡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገዱ አንዳርጋቸው የተናገረው ንግግር በጣም አደገኛ ነው። መሬቱም ውሀውም ግድቡም የኛ ነው ማለት የግብፅን የውሀ ባለቤትነት መካድ ነው ሲሉ የወቀሳ ሙከራ አሰምተዋል መጨረሻ አካባቢ የፖለቲከኞቹ ውይይት ወደ ጦፈ ክርክርና መወነጃጀል የተቀየረ ሲሆን የግብጹ ፖለቲከኛ ሱዳን በአባይ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፋ የግብፅ ህዝብ በውሀ ጥም እንዲሞት እያመቻቸች ነው ብለዋል፡፡

በዚህ መሀከል የሱዳኑ እንግዳ ግብረ መልስ የሰጡ ሲሆን ግብፅ አንድም ቀን ለሱዳን ጥሩ አስባ አታውቅም። ደቡብ ሱዳን ከሱዳን እንድትገነጠል ከአሜሪካ ጋር ወግና ስትሰራ የኖረችው ግብፅ እንጅ ኢትዮጵያ አይደለችም። በማለት በቅርቡ ሱዳን ላይ የፖለቲካ አለመግባባት ሲፈጠር ግብፅ የሱዳንን ህዝብ እርስበርስ ለማጨፋጨፍ በሚዲያዋ ፕሮፓጋንዳ ስትረጭ እንደነበር አጋልጠዋል፡፡.