አባይ ሚዲያ የካቲት 30፤2012

መንግሥት የህዝብ አንድነት እንዲሸረሸር በሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙሃን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ በትላንትናው እለት ማርች 8 አስመልክቶ ኦፌኮ በአዲስ አበባ ባካሄደው ውይይት ከአዳማ የመጣቸው አንዲት ሴት ተናጋሪ ኦፌኮን ወክላ “ከዚህ በኋላ ወንዶች የሀበሻን ሴት ማግባት የለባችሁም፣ ያገቡትንም እያፋታን ነው፣ ከዚህ በኋላ ፍቱ፣ ነፍጠኛ ማግባት የለባቹም” ስትል ተደምጣ ነበር፡፡

ለመስማት የሚዘገንኑ ንግግር አድርጋ ስትጨርስ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና እና አቶ በቀለ ገርባ አጨብጭበውላት ነበር ይህንን ንግገሯን በቀጥታ ያስተላለፈውን የኦ.ኤም.ኤን ቴሌቪዥን ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ድረገጾች ብዙዎች ሲቀባበሉት እና የልጅቷን ንግግር ሲያወግዙት ተስተውሏል፡፡

ይህንን ተከትሎም የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት፥ በህዝባዊ መድረኮችና መገናኛ ብዙሃን በኩል የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮች በሃገር አንድነትና አብሮነት ላይ አደጋ ይደቅናሉ።

ከዚህ አንጻርም መንግስት በመሰል ድርጊት በሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመገናኛ ብዙሃን ላይ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንና ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን ተገቢና ተመጣጣኝ ዕርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ አስታውቀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በትናንትናው ዕለት ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በተመለከተ በአዳማ ከተማ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) ባዘጋጀው መድረክ በ”ኦ ኤም ኤን” (OMN) አማካኝነት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌን የጣሰና ኢትዮጵያዊ ዕውነታን ያላገናዘበ የጥላቻ ንግግር ለዘመናት በአብሮነት ወደኖሩ ህዝቦች መተላለፉን ተከትሎ ፓርቲውም ሆነ የመገናኛ ተቋሙ ተገቢውን ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የተፈጠረው ነገር ስህተት ብቻ ሳይሆን ጥፋት መሆኑንም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል አቶ ንጉሱ መንግሥት ለረጅም ጊዜ በመማማርና መመካከር ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴን አማራጭ አድርጎ በትዕግስት መቆየቱን አንስተዋል።

አሁን ግን በሃገሪቱ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ተግባራት በግልፅ እየተበራከቱ በመምጣታቸው መንግስት እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር ነው የገለፁት።

የኦ.ኤም.ኤን ሚዲያ በበኩሉ በቀጥታ ላስተላለፈው ተናጋሪዋ ያቀረበችውን ንግግር በጊዜው አብዛኛው እንደ ቀልድ ወስዶት የነበረ ቢሆንም እንዲህ አይነት ያልተገባ ንግግር በማስተላለፋችን ይቅርታ እንጠይቃለን በማለት ተንቀሳቃሽ ምስሉን ከድረገጻቸው አጥፍተውታል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በበኩሉ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩና ቁርሾ የሚፈጥሩ ሃሳቦችን በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙሃን ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር ገልጿል።