አባይ ሚዲያ መጋቢት 1፤2012

በመንዝ ጌራ መሐል ሜዳ ትናንት ምሽት በተፈጸመ ጥቃት አራት ሰዎች ተገደሉ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ጌራ ወረዳ ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ በተፈጸመው ጥቃት የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ አስራ ስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የወረዳው ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ሰኞ ምሽት አንድ ሠዓት ከሩብ ላይ ኤፍ ዋን በተባለ የእጅ ቦንብ፣ በሽጉጥና በጩቤ በተፈጸመው ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ በአስራ ስድስት ሰዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል ጉዳት መድረሱን የመንዝ ጌራ ወረዳ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ጌትነት አጎናፍር ተናግረዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው መሐል ሜዳ ከተማ ቀበሌ ሦስት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለ አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ በነበሩ ሰዎች ላይ ሲሆን እስካሁን ማንነቱ ያልታወቀው ጥቃቱን ፈጻሚ ከሞቱት ሰዎች ሁለቱ በሽጉጥ በተተኮሰባቸው ጥይት ሲሆን አንደኛው ደግሞ ግለሰቡ ባፈነዳው ቦንብ እንደሆነ ተነግሯል።

ግለሰቡ በመጠጥ ቤቱ ውስጥ በነበሩ ሰዎች ላይ ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላም መንገድ ላይ ያገኘውን ወደ ቤቱ ሲያመራ የነበረን የ16 ዓመት ታዳጊን በጩቤ በፈጸመበት ጥቃት ክንዱ ላይ ጉዳት ባመድረስ እንዳቆሰለውም አቶ ጌትነት ተናግረዋል።

በጥይትና በቦምብ ጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል ሦስቱ ወዲያውኑ ህይወታቸው እንዳለፈ ከአካባቢው ነዋሪዎች ያረጋገጡ ሲሆን፤ የመቁሰል ጉዳት ከደረሰባቸው 16 ሰዎች መካከል ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ስድስቱ እዚያው ሃኪም ቤት ተኝተው ህክምና እያገኙ ሲሆን ሦስቱ ግን ለተጨማሪ ህክምና ወደ ደብረ ብርሐን መላካቸውን ኃላፊው አረጋግጠዋል።

የተቀሩት ደግሞ ቀላል ጉዳት በመሆኑ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ አግኝተው ወደቤታቸው መመለሳቸው ተነግሯል።

አቶ ጌትነት አጎናፍር አክለውም ክስተቱ ከዚሁ ጋር እንደሚያያዝ ለጊዜው ያልተረጋገጠ ቢሆንም በተመሳሳይ ሰዓት እዚያው መሐል ሜዳ ከተማ ውስጥ አንድ ግለሰብ ጭንቅላቱ ላይ በመጥረቢያ ተመቶ ሞቶ መገኘቱን ገልጸዋል።

በሟቹ ግለሰብ በኪሱ ውስጥ ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያም ሆነ መረጃ ባለመገኘቱ እስካሁን ማንነቱን ለመለየት እንዳልተቻለ ተናግረዋል። ግለሰቡ ተገድሎ የተገኘበት ቦታ በቦምብና በጥይት ጥቃት ከተፈጸመበት አካባቢ ቢያንስ በአንድ ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ የሚገኝ እንደሆነም ታውቋል።

ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ሸሽቶ ያመለጠ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ፖሊስና የአካባቢው የጸጥታ አካላት መንገዶችን ተዘግተው ፍተሻ በማድረግ ወንጀለኛውን ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ጌትነት  ተናግረዋል።