አባይ ሚዲያ መጋቢት 1፤2012

የጀጎል ግንብ አጥር በሶስት ቦታዎች የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል በአለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል ግንብ አጥር እየፈረሰ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ከከፋ ጉዳት እንዲታደገው ነዋሪዎችና በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎች ጠየቁ።

በቱሪዝም ዘርፍ የገቢ ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው የጀጎል ግንብ መፈራረስ ከጀመረ ሶስት ዓመታት እንዳለፈው የገለፁት በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩት አቶ አብዲ አደም ናቸው።

ለአጥሩ መፍረስ ዋናው ምክንያት በውስጡ አለአግባብ የሚለቀቀው ፍሳሽ ዋናው መሆኑን ገልጸው ቅርሶቹን ለትውልድ ለማስተላለፍ ትኩረት ተሰጥቶ ጥገና እንዲደረግለትም ጠይቀዋል።

በክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ የቅርስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ነቢል በክሪ የጀጎል ግንብ አጥር የመፍረስ አደጋን ለመታደግ 5 ሚሊዮን ብር በመመደብ በጥናት ላይ የተመሰረተ የጥገና ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።