አባይ ሚዲያ መጋቢት 2፤2012

በሞረትና ጅሩ ወረዳ እነዋሪ ከተማ ነጻ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የሄደ ቡድን ላይ ጥቃት ደረሰ በአማራ ክልል ሞረትና ጅሩ ወረዳ፣ እነዋሪ ከተማ ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሊሰጡ የመጡ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች የሐይማኖት ስብከት ለምን ያካሂዳሉ በሚል ጥቃት እንደደረሰባቸው የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ተናገሩ።

ወደ ከተማዋ ያቀናው የሕክምና ቡድን 18 የውጪ አገር ዜጎች የተካተቱበት ከ200 በላይ አባላት ያሉት መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር ወጋየሁ ቦጋለ  ገልፀዋል የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ፕሬዝዳንት የሆኑት መጋቢ ይልማ ሙሉጌታ በበኩላቸው በእነዋሪ ከተማ ለ20 ዓመት የነበረ ቤተ ዕምነት ላይ ጥቃትና ዘረፋ መፈፀሙን አረጋግጠዋል።

መጋቢ ይልማ አክለውም ጥቃቱ የተፈፀመው በሐይማኖት አክራሪዎች ነው ያሉ ሲሆን ንብረቶች መዘረፋቸውን፣ ሦስት ሰዎች ተደብድበው ሆስፒታል እንደሚገኙና ቃጠሎ መፈፀሙን ተናግረዋል።

ዋና ኢንስፔክተር ወጋየሁ እንዳሉት የሕክምና ቡድኑ በከተማዋ ነጻ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የመጣው ባለፈው ቅዳሜ እለት ነው ቡድኑ የሕክምና አገልግሎቱን ሊሰጥ የመጣው ከእሁድ እስከ አርብ ድረስ ሲሆን ከጤና ጣቢያው ጎን ድንኳን በመጣል ሐይማኖታዊ ስብከት ሲያካሄዱ እንደነበር ይናገራሉ።

የከተማው ነዋሪ ይህ ለምን ይሆናል ብሎ ተቃውሞ ነበር ያሉት በሰሜን ሸዋ ዞን የሞረትና ጅሩ ወረዳ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳኜ አምታታው  የሕዝቡን ቅሬታ ይዘው ስብከቱን እንዳያደርጉ ለማነጋገር መሞከራቸውን አስታውሰዋል።

ዋና ኢንስፔክተሩ በበኩላቸው ሕዝቡ የሐይማኖት ስብከቱ በከተማዋ በሚገኘው የፕሮቴስታንት የእምነት ተቋም ቅጽር ግቢ ቢሰጥ  ችግር የለብንም ማለቱን በማነሳት፤ ከጤና ጣቢያው ጎን ድንኳን ጥለው ስብከት ማካሄዳቸውና የሐይማኖት መጻህፍት ማደላቸው ቁጣን እንደቀሰቀሰ አመልክተዋል።

ዋና ኢንስፔክተር ወጋየሁ አክለውም ከእሁድ ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ አገልግሎቱ በሰላም ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም በኋላ ግን ከገጠር ቀበሌዎችና ከከተማው ተቆጥተው የመጡ ወጣቶች በድንኳኑ እንዲሁም በሙሉ ወንጌል ቤተ እምነት ላይ የድንጋይ ድብደባና ቃጠሎ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልፀዋል።

አቶ ዳኜ በበኩላቸው “የተቆጣው ሕዝብ ከቁጥጥር ውጪ ነበር የሆነው” በማለት በወቅቱ ጉዳት ሳይደርስ ችግሩን ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን ይገልፃሉ።

ዋና ኢንስፔክተር ወጋየሁ አክለውም ዋነኛ ትኩረታችን የነጻ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ወደ ከተማችን የመጡ ባለሙያዎችና ባልደረቦቻቸው ምንም አይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው መከላከል ነበር፤ ያንንንም ማድረግ ችለናል በማለት ቡድኑን እስከ ደብረብርሃን ድረስ አጅበው በመሸኘት እንዲሄዱ ማድረጋቸውን ይገልፃሉ።

ትናንት በነበረው አለመረጋጋት አንድ የጥበቃ ሰራተኛ በድንጋይ ጉዳት እንዳጋጠመው፣ ስብከት ሲካሄድነበት የነበረ ድንኳን፣ እንግዶቹ ለመቆያ የሰሩት ካምፕና ልብስ እንዲሁም የሙሉ ወንጌል የቀድሞ ቢሮዎች መቃጠላቸውን ዋና ኢንስፔክተሩ ጨምረው ገልፀዋል።

ዋና ኢንስፔክተሩ አክለውም እስከአሁን ድረስ በጉዳዩ ተጠርጥሮ የተያዘ አንድም ግለሰብ እንደሌለ በመግለጽ ክትትል እያደረጉና መረጃ እያሰባሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።