አባይ ሚዲያ መጋቢት 07፤2012

የግብጽ የተሳሳተ አቋም ለስምምነቶች አለመሳካት ምክንያት ሆኗል ተባለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ‹‹የህዳሴው ግድብ ድርድር ተግዳሮትና ቀጣይ አቅጣጫ›› በሚል ርዕስ ላይ በተካሄደው ውይይት እንደተገለፀው፤ በህዳሴ ግድብና በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል የሚካሄዱ ውይይቶች የሚፈለገውን ያህል ውጤት ያልተገኘበት ዋነኛ ምክንያት ግብፅ በተፋሰሱ ላይም ያላት የተሳሳተ አቋም መሆኑ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፖለቲክስ ተመራማሪና መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ፤ ግብፅ በግድቡ ላይ እያሳየች ያለችው አቋም በተፋሰሱ ላይ የበላይ ልሁን ከሚል እሳቤ እና የሌላውን ፍላጎት ካለማክበር የመነጨ መሆኑን አስረድተዋል።

ግብፆች «የአባይ ጉዳይ ለድርድር አይቀርብም» የሚል አቋማቸው ካልተለወጠ በቀር ለእነሱም ሆነ ለሌሎቹ የተፋሰሱ አገራት የጋራ ተጠቃሚነት ፈቃደኛ ሆነው ለድርድር የሚቀርቡበት አጋጣሚ አነስተኛ መሆኑን ይጠቁማሉ።

በተለይ በተፋሰሱ ላይ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ካለእኔ ፈቃድ ሊተገበሩ አይገባም የሚለው የግብፅ አቋም ዘመኑን ያላገናዘበና የዓለም አቀፍ ሕግን የሚፃረር መሆኑ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለችው ግድብ በተፈጥሮ ሀብቷ የመልማት መብትን የተከተለና ዓለም አቀፍ ሕግን ያልተቃረነ መሆኑን የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ፤ ግድቡ የውሃ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ከሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑንም አመልክተዋል።

በውይይቱ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ሕግ ተመራማሪ ዶክተር ደረጀ ዘለቀ፤ የግብፅ አቋም መነሻ በአባይ ወንዝና በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ዘመናትን የተሻገረ «የውሃው ባለቤት እኔ ነኝ» ከሚል የተሳሳተ እሳቤ የተወለደ መሆኑን ገልጸዋል።

ግብፅ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ እንደ መከራከሪያ የምታነሳቸው የቀድሞ ስምምነቶች የውሃውን ኢፍትሃዊ ክፍፍል በግልፅ የሚያመላክቱ ዓለምአቀፍ የሕግ ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው።

በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የሚደረጉ ስምም ነቶች ሁሉ ውጤት የሚያጡት በግብፅ አቋም መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ደረጀ፤ ሌሎች ሀገራት በተፈጥሮ ሀብታቸው የመልማት ሙሉ መብት እንዳላቸውና ግብፅም አቋማን ልትፈትሽ እንደሚገባ ይመክራሉ።

ለትብብር ተማፅኖ ማቅረብ የነበረባት ግብፅ፣ በአንፃሩ የትብብር መንፈስን የሚንዱ አቋሞችን በማራመድ ላይ መሆኗን ገልፀው፤ ግብፅ የያዘችው አቋም የተቃረነ በመሆኑ በተፋሰሱ ላይ የሚሰሩትን ፕሮጀክቶች በቀናነት ተመልክታ የጋራ አሸናፊነት መርህ ልትከተል ይገባታል ሲሉ ዶክተር ደረጀ መክረዋል።

ግብጽ በተሳሳተ አቋም ላይ ብትገኝም ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ግድብ አጠናክራ መቀጠል ይገባታል ያሉት ምህራኑ፤ አሁን ላይ በግድቡ ዙሪያ የያዘችው አቋም ላይ መፅናት እንደሚገባትም ሀሳብ ሰንዝረዋል።