አባይ ሚዲያ መጋቢት 9፤2012

በህዳሴ ግድብ ግንባታ በሚሳተፉ የውጭ ደርጅቶች ላይ ጫና ለመፍጠር የተጠራው የግብፅ ፓርላማ ሳይሰበሰብ ቀረ፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በማከናወን ላይ የሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፏቸውን አቋርጠው እንዲወጡ የተጠራው የግብፅ ፓርላማ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ስብሰባ፣ በኮሮና ቫይረስ ሥጋት ሳይካሄድ ቀርቷል።

የግብፅ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በህዳሴ ግድቡ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ ለማክሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. መጥራቱን፣ የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበው ነበር።

የውጭ ጉዳይ ኮሚቴው ሊቀመንበር እንደገለጹት፣ የኮሚቴው ስብሰባ በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ የሚሳተፉ የውጭ ድርጅቶች ጥለው እንዲወጡ የግብፅ መንግሥት ማድረግ ያለበትን ጫና በተመለከተ መምከር የስብሰባው አጀንዳ ነበር።

አንድ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊ ግን የግብፅ ፓርላማም ሆነ የግብፅ መንግሥት ግድቡን በተመለከተ ከሚጠቀሙባቸው ቴክኒኮች መካከል አንዱ፣ በሚዲያ ዘመቻ ሥጋት የመፍጠር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ የሚዲያ ዘመቻ እንደማያሳስብና ተግባራዊ መሆን የማይችል ነው ሲሉም አጣጥለውታል።

በህዳሴ ግድብ የሚሳተፉ ኩባንያዎች በግብፅም በተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚሳተፉ ስለሆኑ፣ ውላቸው እንዲቋረጥና ወደፊት እነዚህ ኩባንያዎች ምንም ዓይነት ፕሮጀክት በግብፅ እንዳያገኙ ማድረግ እንደሚገኝበት ከግብፅ በኩል ተሰምቷል።

በተጨማሪም የዓለም ባንክና ሌሎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች እነዚህ ኩባንያዎች እንዳይሳተፉ ለማድረግ፣ የግብፅ መንግሥት ከገንዘብ ተቋማቱ ጋር እንዲነጋገር ማድረግ የሚለውም ይገኝበታል።

ይሁን እንጂ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ በግብፅ በመስፋፋቱ ምክንያት፣ የተጠራውን አስቸኳይ ስብሰባ ማካሄድ እንዳልተቻለና ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መደረጉን የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

የግብፅ ፓርላማ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ዕቅድን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊ ይህ ኢትዮጵያን የሚያሳስብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ግብፆች ለማድረግ የማይፈልጉት ነገር እንደሌለ የተናገሩት እኚህ ኃላፊ፣ አሁን ያሰቡትን ድርጊት ለመፈጸም አቅቷቸው እንጂ ግድቡ ሲጀመርም የጣሊያኑን ኩባንያ ሳሊኒን ለማስወጣት ያላደረጉት ሙከራ እንዳልነበር ገልጸዋል።

ከሳሊኒ ውጪ በግድቡ ግንባታ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ዋነኞቹ ኩባንያዎች በሜቴክ ሥር በንዑስ ተቋራጭነት ላለፉት ዓመታት ሲሳተፉ እንደነበር፣ ግብፅ እነዚህ ኩባንያዎችን ማስወጣት ብትችል ኖሮ ቀደም ባሉት ዓመታት ይሳካላት እንደነበር ኃላፊው ጠቁመዋል።

የግብፅ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ሙከራዎችን የሚያደርገው በድብቅ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው፣ ‹‹ኩባንያዎቹን ማስወጣት እንደማይቻል ሲያውቁት፣ ቢያንስ በሚዲያ ሥጋት እንፍጠር ብለው የለቀቁት መረጃ ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል።