አባይ ሚዲያ መጋቢት 10፤2012

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ግብፅ ለዘመናት በአባይ ወሃ ላይ ያላት የባለቤትነት ስሜት እስከተቀየረ ድረስ ድርድሩ ውጤት ያመጣል አሉ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ከታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ጋር ለመነጋገር የሚያስችላትንና የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር ረቂቅ የውይይት ሰነድ ማዘጋጀቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ::

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ምሁራንና ባለድርሻ አካላት እየመከሩበት የሚገኘው ይኸው ረቂቅ ሰነድ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ የህዳሴውን ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን ብቻ የሚመለከት እንዲሁም ኢትዮጵያ ድርድር የማታደርግባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ለይቶ ያስቀመጠ ሲሆን በውይይት ዳብሮ እንደተጠናቀቀ በአገራቱ መካከል የተቋረጠውን ውይይት ለማስቀጠል አማራጭ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል ብለዋል::

ግብፅ ለዘመናት በአባይ ወሃ ላይ ያላት የባለቤትነት ስሜት እስከተቀየረና የሌሎች አገራትንም ውሃውን በፍትሃዊነት የመጠቀም ህጋዊ መብት እስካከበረች ድረስ ውይይቱ አሁንም ውጤት ያመጣል የሚል እምነት አለኝ ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሰላማዊ ውይይትና ድርድር ውጪ ሌላ አማራጭ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንደማያመጣም አሳስበዋል::

ከዚህ ሌላ ግብፅ የግድቡን ግንባታ በልዩ ልዩ መልኩ ለማስተጓጎል እየሄደችበት ያለው መንገድ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ሃብቷን በህጋዊ አግባብ እንዳትጠቀም የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት በጨለማ ኑሮዋቸውን የሚገፉ ከ 65 ሚልዮን የሚልቁ የአገሪቱን ዜጎች መሰረታዊ ችግር እንዳይፈታ መሰናክል የሚፈጥርና የጀመረችውን የኢንዱስትሪና ልማት መዳረሻ ጉዞም የሚያደናቅፍ በመሆኑ ፈፅሞ ተቀባይነት አይኖረውም ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ::

ኢትዮጵያውያን በአንድነት ዘብ ቆመው ለአገሪቱ መፃኢ ልማትና ዕድገት ወሳኝ የሆነውን የግድቡን ግንባታ ለማስጓጎል የሚያሴሩትን ሁሉ አጥብቀው እንዲታገሉና በአገር ውስጥም በዲያስፖራም የሚገኙ ዜጎች ሁሉ በሙያ በገንዘብና በጉልበት ለግድቡ ግንባታ ስኬት የጀመሩትን ጥረት እንዲያጠናክሩም መልዕክት አስተላልፈዋል::