አባይ ሚዲያ መጋቢት 10፤2012

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ሃላፊ አቶ ነብዩ ስሁል ህወሃት የጥቅምና የስልጣን ጥያቄ ነው ሲሉ ገለጹ ከቀናት በፊት የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ቅርንጫፍ ሃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ ነብዩ ስሁል ከሹመታቸው በኋላ ከአዲስዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ለትግራይ ህዝብ ብልጽግና እንጂ ህወሃት እንደማያስፈልገው በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

ሃላፊው ኢትዮጵያን የምገልጸው መሰረቱ ጽኑ በሆነ ቤት ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ደግሞ የቤቱ መሰረት ነው ያሉ ሲሆን ህወሓትም ሆነ የአገዛዙ ባህሪ ሲታይ የኢትዮጵያንም ሆነ የትግራይን ህዝብ ስነ-ልቡና ያልተገነዘበ፤ ከየት እንደመጣ ያልለየ ሊባል የሚችል አይነት ስነ-ልቡና ይዞ የመጣ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

በኔትወርክ በቡድን ተደራጅተው አገር ሲዘርፉ የቆዩ ሰዎች እንዳሉ ማንም የሚያውቀው ሀቅ ነው ያሉት አቶ ነብዩ ስለዚህ መሰረታዊ ልዩነቱ መታየት አለበት፤ ህውሃትና የትግራይ ህዝብ የተለያዩ ናቸው አንድ ሊሆኑ አይችሉም ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ነብዩ አክለውም ዘር የፖለቲካ መዘውር አድርጎ መጠቀምና ፖለቲካን ደግሞ ዘር አድርጎ መቀጠል አይቻልም፡፡ ይህ ምናልባት አንዳንድ የተፈጠሩ ክፍተቶችን ለማረም ልትጠቀም ትችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን አገር ለመገንባት፤ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ግን በፍጹም አያስችልም በማለት አብራርተዋል፡፡

አቶ ነብዩ ስሁል ስርዓቱ የአፓርታይድ ስርዓት እስኪመስል ድረስ የዘር ፖለቲካው ቀጥሎ እስከ ቀበሌና መንደር የዘለቀ ህዝብን የመከፋፈል ስራ ሲሰራ ቆይቷል በማለት ባለፉት27 ዓመታት ብቻ ነው በህወሓት መሪነት በሴራ ፖለቲካ የትግራይ ህዝብ ለአገር ያለው ተቆርቋሪነት ያነሰ እንዲመስል ሆኖ የተሳለው እንጂ የትግራይ ህዝብ አገራዊ ራዕይ ያለው አገር እየፈጠረና አገር እየገነባ የኖረ ህዝብ ነው ብለዋል፡፡

ህወሓት የሚያነሳው የመስመር ጉዳይ ሳይሆን የጥቅም፣ የበላይ የመሆንና የስልጣን ጉዳይ ነው ያሉት አዲሱ የትግራይ ብልጽግና አመራር ከዚህ በኋላ ግን ኢትዮጵያ የአንድ ቡድን፣ የአንድ ብሄር ወይም አካባቢ ልዕልናን ያነገሰች ልትሆን አትችልም በማለት ያክላሉ፡፡

ሃላፊው መጠየፍ ካለብን አሃዳዊ ተብሎ ሊፈረጅና ሊወገዝ የሚገባው እንቅስቃሴ ካለ ህውሃት የተንቀሳቀሰበት መንገድ ነው ያሉም ሲሆን  በተለይ በትግራይ የአንድ አካባቢ የበላይነት ተፈጥሮ አስተዳዳሪዎች እኛ ብቻ ነን የሚል ተፈጥሮ የፌዴራል ስርዓቱ በከፋ ደረጃ እንዲተገበር ተደርጓል በማለት ይወቅሳሉ አቶ ነብዩ የትግራይ ህዝብ ለራሱ ፍትህ የሚፈልግ በጣም የተጨቆነ ህዝብ ነው፤ የህወሀት አመራሮችን ነጥለን ነው መታገል ያለብንም ብለዋል፡፡