አባይ ሚዲያ መጋቢት 12፤2012

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ‹‹ ብልጽግና ፓርቲ››ከፍተኛ ገንዘብ ማሰባሰቡ ስጋት እንደማይሆንባቸው ገለጹ ብልፅግና ፓርቲ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ራሱን በሃብት እና በገንዘብ ማበልጸጉ ስጋት አንደማይሆንባቸው የገለጹት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ፣ የፓርቲው ገንዘብ እና ድጋፍ የማሰባሰብ ሂደት የምርጫውን ውጤት እንደማይወስነው ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ብልጽግና ባካሄደው የሀብት ማሰባሰብ እንቅስቃሴ 1.5 ቢሊየን ብር ማግኘቱ ይታወሳል ከወራት በፊት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባዘጋጀው የራት ፕሮግራም ፓርቲያቸው ጠቀም ያለ ሀብት ማሰባሰበሱን የገለጹት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ፣ እንዲህ ያሉ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ለፓርቲዎች የምርጫ እንቅስቃሴ በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ናትናኤል አክለውም ዜጎች በአስገዳጅ ሁኔታ ገንዘባቸውን የሚሰጡ ከሆነ ግን ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት አያስችልም፤ በዚህ ረገድ የመንግስት ባለስልጣናት ለፓርቲያቸው ድጋፍ የሚያሰባስቡበት መንገድ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ገንዘብ ማሰባሰቡን በተመለከተ ግልጽ መመሪያ ማዘጋጀት እንዳለበት አቶ ናትናኤል ገልጸዋል የብልጽግና ፓርቲ ሀብት ምናልባት ለህዝብ ሃሳብን ለማድረስ አቅም ሊሆነው ይችላል፣ ነገር ግን የምርጫውን ውጤት ከወዲሁ የሚወስን አይሆንም ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ የመንግሥትን መዋቅር በመጠቀም እና ነዋሪዎችን በማስገደድ ገንዘብ ማሰባሰብ መቀጠሉን የሚያስረዳ የሰነድ ማስረጃ ኢዜማ እንደደረሰው ማስታወቁ ይታወቃል።

ኢዜማ የደረሰው የሰነድ ማስረጃ እንደሚያትተው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ሠራተኛና ማኅበራዊ ጽሕፈት ቤት ለነዋሪዎች በላከው ደብዳቤ ላይ የብልፅግና ፓርቲ እያከናወንኩት ላለሁት የልማት ተግባራት ነዋሪዎች የገንዘብ መዋጮ አድርጉ በማለት የሚያዝ ሲሆን ከ1000 ብር በላይ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው እና እስከ መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ገቢ እንዲያደረግ የሚያሳስብ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ የኦፌኮ፣ የመኢአድ እና የኢዴፓ አመራሮችም የኢዜማን ሃሳብ ይጋራሉ እስከ አሁን የተጠናከረ የገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ አለማከናወናቸው የገለጹት ፓርቲዎቹ፣ ምርጫው ላይ ገንዘብ ጉልበት ቢኖረውም የምርጫውን ውጤት ለህዝብ የማቅረብ የፖለቲካ ፕሮግራም ሃሳብ እንደሚወስነው ተናግረዋል፡፡