አባይ ሚዲያ መጋቢት 13፤2012

ፓርላማ በህዳሴ ግድብ ላይ ለመነጋገር የያዘው ስብሰባና ጉብኝት በኮሮና ሥጋት ተላለፈ ፓርላማው በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ከግብፅና ከሱዳን ጋር በአሜሪካ ተጀምሮ የነበረውን የህዳሴ ግድብ ድርድር አስመልክቶ ማብራሪያ ለመስማት ያቀደ ቢሆንም፣ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በወጣው የመንግሥት መመርያ ምክንያት ስብሰባው ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ከኃላፊዎች ታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መግባቱ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባሉት ቀናት፣ አስራ አንድ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል መንግሥትም የበሽታውን ሥርጭት ያግዛሉ የተባሉ የመከላከል ዕርምጃዎችንና መመርያዎችን ቀደም ብሎ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ የትምህርት ተቋማትን በጊዜዊነት መዝጋትን፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ ስብሳባዎችንና የቡድን ኩነቶችን መገደብ ያካትታል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት መካሄድ የነበረባቸውን ሁለት መደበኛ ስብሰባዎቹን በጽሕፈት ቤቱ አማካይነት፣ ለሁሉም ተመራጭ የምክር ቤቱ  አባላቱ መደበኛ ስብሰባዎች እንደማይካሄድ ማስታወቁ ይታወሳል፡ከተለያዩ የጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ለማወቅ እንደተቻለው፣ ከሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለማካሄድ ቀደም ብሎ የተዘጋጁ የቋሚ ኮሚቴዎች መደበኛ ስብሰባዎችና ሁለት አስቸኳይ ስብሰባዎች ተሰርዘው ለሌላ ጊዜ መተላለፋቸው ተረጋግጧል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው በህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ሊመክር ታስቦ የነበረው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ትልቅ ግምት ተሰጥቶት ነበር ተብሏል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ስብሰባው በዚህ ሳምንት ለመጥራት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዋናነት የውጭ ጉዳይ፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም በህዳሴው ግድብና በዓባይ ውኃ አጠቃቀም በድርድሩ ተሳታፊ የነበሩ ባለሙያዎችን ለመጥራት ተዘጋጅቶ እንደነበር የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ተስፋዬ ዳባ አረጋግጠዋል፡፡

የተሰረዘው አስቸኳይ ስብሰባ ሌላ ጊዜ ሊካሄድ እንደሚችል ቢገልጹም፣ ትክክለኛ ተለዋጭ ቀኑ መቼ ሊሆን እንደሚችል ግን እርግጠኛ አለመሆናቸውን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል አቶ ተስፋዬ፣ በመጪው ሳምንት የሁሉም ቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎችንና የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችን ያቀፈ በአፈ ጉባዔው የሚመራ ቡድን፣ ወደ ህዳሴው ግድብ ሊያደርገው የነበረ የመስክ ጉብኝት መሰረዙንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡