አባይ ሚዲያ መጋቢት 13፤2012

ኢትዮጵያ ሁለት ተጨማሪ የኮቪድ 19 ተማሚዎች ማግኘቷን አረጋግጣለች የመጀመሪያው ከቤልጂየም የመጣ የ28 ዐመት ኢትዮጵያዊ ሲሆን ሁለተኛው ከዱባይ የመጣ የ34 ዐመት ኢትዮጵያዊ ነው።

የ28 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ በሽታውን ሪፖርት ወደ አደረጉ አገሪት ቤልጂየም እና ኔዘርላንድስ ተጉዞ የነበረ እና መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የገባ ነው ተብሏል፡፡

ታማሚው ወደ ሀገር ከገባበት ዕለት ጀምሮ ራሱን በመለየት የጤናውን ሁኔታ ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ÷ የበሽታውን ምልክት በማሳየቱ ባደረገው ጥቆማ ናሙና ተወስዶ በላብራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዙ መረጋገጡ ተገልጿል፡፡

ሁለተኛው የ34 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ መጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሚደረገው የመንገደኞች የሙቀት ልየታ÷ የኮሮና ቫይረስ ምልክቶች በማሳየቱ በለይቶ ማቆያ እንዲቆይ በማድረግ በላብራቶሪ ምርመራ በኮረና ቫይረስ መያዙ ተረጋግጧል፡፡

ይህ እስከ አሁን የተረጋገጡ የኮቪድ 19 ተጠቂዎችን ቁጥር ወደ 11 አድርሶታል እስካሁን በሽታው እንዳለባቸው ከተረጋገጡት ሰዎች 4ቱ ጃፓናዊያን፣ 5ቱ ኢትዮጵያዊያን፣ 1ዷ እንግሊዛዊት እና 1ዱ ኦስትሪያዊ ናቸው።

ከዛሬ ዕኩለ ሌሊት ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች በስካይ ላይት እና ጊዮን ሆቴል በተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ ሆቴሎች ውስጥ ለሁለት ሳምንታት እንዲቆዩ የሚያስገድደው ትዕዛዝ ተግባራዊ ይሆናል።

ኮሮና በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ41 አገራት ተከስቶ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ 37 ሰዎችን ገድሏል የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል በድረገጹ ዛሬ ባወጣው መረጃ መሰረት የተጠቂዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ይጨምራል።

አገራት ቫይረሱን ለመቆጣጠር እጅግ ፈጣን እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባቸውም አሳስቧል ግብጽ፣ደቡብ አፍሪካ እና አልጀሪያ በአንጻራዊነት ከፍተኛ ህዝብ የተጠቃባቸው አገራት ሲሆኑ ዩጋንዳ የመጀመሪያውን የኮሮና ተጠርጣሪ ዛሬ ይፋ አድርጋለች።

በአለማቀፍ ደረጃ ደግሞ ቫይረሱ እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ 308 ሺህ 592 ሰዎቸን ሲያጠቃ 95 ሺህ 829 ያህሉ ሲያገግሙ 13 ሺህ 69 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል በቫይረሱ ብዙ ዜጎች ከሞቱባቸው አገራት ውስጥም በጣልያን 4 ሺህ 825 ሰዎች፣በቻይና 3 ሺህ 261 በኢራን 1 ሺህ 556 እንዲሁም በስፔን 1 ሺህ 381 ሰዎች ሞተዋል።

በሌላ በኩል እንደ የአለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ILO ግምት ከሆነ የኮሮና ወረርሽኝ ከጤና ጉዳቱ ባሻገር መንግሥታት በፍጥነት እርምጃ ካልወሰዱ እና ለሰራተኞች ድጋፍ ካላደረጉ በአለም ዙሪያ እስከ 25 ሚሊዮን የሚደርሱ ስራዎች ሊታጡ ይችላሉ።